የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የደሞዝ ጭማሪ እና የተለያዩ የመብትና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ከትናንት ጀምሮ በየትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ተቃውሞዎችን ሲያደርጉ የነበሩት መምህራን፣ በዛሬው እለት አድማቸውን ያቋረጡት ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከወላጆችና ተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይዒት መሰረት ነው።
የወረዳው ባለስልጣናት መምህራኑ ካደረጉት ህገወጥ የስራ ማቆም አድማ የፖለቲካ እጅ እንዳለበት ቢናገሩም፣ ይህን አይነቱን ፍረጃ የተቃወሙ አንዳንድ መምህራን ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ታውቋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ መምህር ለኢሳት ሲናገሩ የኑሮ ውድነት መባባስ የደሞዝ ጭማሪ እንዲጠየቁ አድርጎዋቸዋል።
የወረዳው የካቢኔ አባላት መምህራንን እና ወላጆችን ለማጋጨት እንዲሁም መምህራንን ለማስፈራራት መኩራ አደርገው እንደነበር መምህሩ::
መምህራኑ ከሙያ ማህበሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ስራ ለመጀመር ቢስማሙም፣ የወረዳ የካቢኔ አባላት ግን መምህራን ይቅርታ ካልጠየቁ ስራ አይጀምሩም የሚል አቋም አራምደዋል።
መምህራን “ይቅርታ የሚያስጠይቅ ምንም ነገር የለም፣ ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት አድማ እድርገናል የሚል መልስ መስጠታቸውን እና በዚህም ውዝግብ ስብሰባው ያለውጤት መበተኑን መምህሩ ተናግረዋል::
መሳሳይ ተቃውሞዎችም በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
በአገሪቱ የሚገኙ መምህራን መንግስት የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርግ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወቃል።
መንግስት ከመምህራን ማህበር ለቀረበለት የደሞዝ ጥያቄ እስከ ጥር 30 ቀን መልስ እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም እስከአሁን መልስ አለመስጠቱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር የሆኑትና ለመምህራን መብት ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት መንግስቱ አህመዴ መታገዳቸውም ታውቋል።
መምህሩ ለመምህራን ጥቅም በመሟገትና የመንግስት ባለስልጣናት መምህሩን የስርአቱ ካድሬ ለማድረግ የሚያደርጉትን ሩጫ ሲቃወሙ ቆይተዋል።