መንግስት የቀድሞ ሰራዊት አባላትን እና በጡረታ የተገለሉ የኢህአዴግ ተቀናሽ ሰራዊትን ለመመለስ ውይይቶችን እያካሄደ መሆኑ ታወቀ

የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት የቀድሞ ሰራዊት አባላትን እና በጡረታ የተገለሉ የኢህአዴግ ተቀናሽ ሰራዊት አባላትን ወደ መከላከያ ለመመለስ ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ውይይቶችን እያካሄደ መሆኑ ታወቀ

በሰሜን ሸዋ ዞን 167 ተቀናሽ የሰራዊት አባላት ሰሞኑን በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ተስብስበው እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የተቀናሽ ሰራዊት አባላት ወደ መከላከያ እንዲመለሱ ከደብር ዘይት አየር ሀይል አባላት የተውጣጡ መኮንኖች ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም ፣ ሁሉም አባላቱ በአንድነት መንግስት ጦርነት ሲኖር ብቻ ነው ወይ የሚፈልገን በሚል ምክንያት ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ወታደሮቹ በርካታ ችግሮችን የዘረዘሩ ሲሆን፣ “አንድ ጊዜ በባድሜ ትምህርት አግኝተናል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ግን አንሞኝም፣ እኛ እንደዜጋ እየታየን አይደለም፣ ጡረታችንን ከፈለጋችሁ መውሰድ ትችላላችሁ” እያሉ በሀይለቃል ይናገሩ እንደነበር በስብሰባው ላይ የተሳተፈ አንድ የተቀናሽ ሰራዊት አባል ለኢሳት ተናግሯል።

መኮንኖቹ “ከኤርትራ ጋር ለሚደረገው ጦርነት አገራችሁን አገልግሉ” የሚል ጥያቄ ለቀድሞ የሰራዊት አባላት እንደቀረቡላቸው ለማወቅ ተችሎአል።

ከፌደራሉ መንግስት ተወክለው የመጡት ባለስልጣኖች ፣ ” ለአገርና ለመንግስት ጸሮች ናችሁ በማለት ወታደሮቹን እንደተናገሩዋቸው፡” አባሉ አክሎ ገልጧል።

መንግስት ወታደሮችን ለመቅጠር በተለያዩ አካባቢዎች ማስታወቂያ ማውጣቱም ታውቋል።