“የብአዴን አባል ካልሆንክ መቀደስ አትችልም ተብዬ ተባረርኩ” ሲሉ አንድ ካህን ተናገሩ

የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-“የኢህአዴግ- ብአዴን አባል ካልሆንክ፤በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ መቀደስ አትችልም ተብዬ ተባረርኩ”ሲሉ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ካህን ተናገሩ።

 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በኖኖ ወረዳ ማሩ ጉቴ በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲኖሩ የነበሩት ቀሲስ ገረመው ናደው ተሰማ፤ ለፍኖተ-ነፃነት እንደተናገሩት ከገዥው ፓርቲ በኩል የቀረበላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጥያቄ አልቀበልም በማለታቸው፤ከቤተ-ክርስቲያን አገልግሎታቸው ከመታገዳቸውም በላይ  በሚደርስባቸው የተለያዬ በደል  ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ዘጠኝ ልጆቻቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።

“አንድ ቀን የአምቦ ሐገረ ስብከት ካህናት ኃላፊ ቄስ ደረጀ ፀጋዬና የዞኑ መስተዳድር ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሙለታ አስጠርተውኝ ‘የብአዴን አባል እንድትሆን”በማለት ጠየቁኝ ያሉት ቀሲስ ገረመው፤ “ እኔ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን አልፈልግም፡፡ በቅስናዬ ማገልገል እፈልጋለሁ፤ መንግስት ከእኔ የሚጠብቅብኝን ግብርና ልማት አሟላለሁ፡፡ በማንም ፖለቲካ ድርጅት ውስጥም አልገባም። የልጆች አባት ስለሆንኩ፤ ልጆቼን ማስተማር እፈልጋለሁ አልኳቸው”ብለዋል።

ይህን ምላሽ ሢሰጧቸው፦“እንግዲያውስ ከዛሬ ጀምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ አታገለግልም!” እንዳሏቸው የገለፁት ቀሲስ  ገረመው፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከ20 ዓመት በላይ ባገለገልኩበት ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል።

ቀሲስ ገረመው ከዚህም በላይ በአካባቢው አስተዳደሮች መሬታቸውን እንደተነጠቁ፣እንደተደበደቡ፣ አጭደው የከመሩት የደረሰ ሰብል እንደተቃጠለባቸውና ሌሎችም በደሎች እንደተፈፀሙባቸው በዝርዝር ተናግረዋል።

“የተፃፈበትን  ወረቀት ያህል እንኳ ዋጋ አያወጣም” የተባለለት የኢህአዴግ ህገ-መንግስት፤ መንግስት በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በዜጎች የግል እምነት ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ፤እንዲሁም ዜጎች ባላመኑበትና ባልፈለጉት ድርጅትና ማህበር ውስጥ አባል እንዲሆኑ የሚያስገድዳቸው ሀይል እንደሌለ ያመለክታል።

 ይሁንና በተጨባጭ የሚታየው እውነታ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ መሆኑንና፤ ዜጎች መብቶቻቸው የሆኑትን የፈለጓቸውን ነገሮች ለማግኘት እንኳ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ መገደዳቸውን ያስተዋሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ገዥውን ፓርቲ በህገ-መንግስት ጥሰት በተደጋጋሚ ሲከሱት ይደመጣሉ።

“ኢህአዴግን ከህግ በላይ ነው”የሚሉ  ታዛቢዎች በበኩላቸው፦”ሌሎች ኩሽ ሲሉት ‘ሊፈርስ ነው’ የሚባለው ህገ-መንግስት፤ኢህአዴግ በዶዘር ሲገፋው አለመነቃነቁ ይገርማል” በማለት ትዝብታቸውን ሲገልጹ ይሰማሉ።