የአረብ ሳት ስርጭቶች የሚታወኩት ከኢትዮጵያ በሚለቀቅ ሞገድ ነው ተባለ

የካቲት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሊባኖስ የኮምንኬሽን ሚኒስትር የሆኑት ኒኮላስ ሽናዊ  የአርብሳት ከፍተኛ ባለስልጣኖችን ጠቅሰው ለዘ ደይሊ ስታር ለተባለው የሊባኖስ ጋዜጣ እንደተናገሩት በአረብሳት የሚተላለፉት ስርጭቶች እየታወኩ ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት ስርጭቱን ለማፈን በሚያደርገው ሙከራ መሆኑን የአረብሳት ባለስልጣናት ለኢትዮጵያ መንግስት የጻፉትን ደብዳቤ አይተው አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት አረብሳትን ለማፈን እንዳስገደደው ሚኒሰትሩ ገልጠዋል።

የሊቢያ እና የግብጽ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አልጀዚራን ጨምሮ በርካታ የአረብ ሳተላይቶች መታፈናቸውን ገልጧል።

የመለስ መንግስት በአረብሳት የሚተላለፈውን የኢሳትን ስርጭት ሲያፍን መቆየቱ ይታወቃል። አረብሳት የመንግስትን ድርጊት ማስቆም ባለመቻሉ ከኢሳት ጋር ያለውን ውል በማቋረጥ፣ ስርጭቱ እንዲቋረጥ አድርጓል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአረብሳት ሲተላለፍ የነበረው የኤርትራ ቴሌቪዥን ከኢትዮጵያ በሚለቀቅ ሞገድ እንዲታፈን ተደርጓል። ብዙዎች እንደሚሉት የኤርትራ ቴሌቪዥን የመታፈን አደጋ የገጠመው የኢሳትን አንዳንድ ስርጭቶች  ማስተላለፍ በመጀመሩ ነው።

አረብሳት ከመለስ መንግስት ጋር በገባው ውዝግብ ሳቢያ፣ በአረብሳት ይተላለፍ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲቋረጥ አድርጓል።

መንግስት የአረብሳትን ሞገድ እንዳለ ለማፈን በሚያደርገው ጥረት፣ በአረብሳት የሚተላለፉት አልጀዚራን ጨምሮ ሌሎች ስርጭቶችም የመታወክ አደጋ ገጥሞዋቸዋል።

7 ሚሊዮን ህዝብ በምግብ ለስራ ፣ 4 ሚሊዮን ህዝብ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ፣ የመለስ መንግስት ስልጣኑን ለማቆየት ሲል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጣ ስርጭቶችን ለማፈን ሙከራ ያደርጋል።

ኢሳት ይህን አፈና ተቋቁሙ ለረጅም ጊዜ በአየር ላይ የሚቆይበትን ስልት እየቀየሰ ነው።