ባለፉት 20 ዓመታት ለደረሰው ጥፋት ዋነኛው ተጠያቂ መለስ ናቸው ተባለ

የካቲት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መለስ ሰሞኑን በፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት፤ መንግስታቸው መዳከሙን የሚያመለክት ነው ያሉት ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ባለፉት 20 ዓመታት ለደረሰው ጥፋት ዋነኛው ተጠያቂም ራሳቸው ናቸው ሲሉ ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ የመድረኩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣የ አንድነቱ አቶ አስራት ጣሴ እና  የ የኢዴፓው አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው።

 አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን  የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት ሪፖርት  ለፓርላማው  ሲያቀርቡ፤ “የአዲሱ  ሊዝ አዋጅ ዋነኛ አላማ የመንግስት ሌባንና የውጪ ሌባን ለመከላከልና ሀብታምም ደሃም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው” በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።
በፓርላማ ከቀረበው ሪፖርት፤ አቶ መለስ ለ21 ዓመት የመሩት መንግስት የሌባ መንግስት መሆኑን ለመታዘብ እንደቻሉ የገለፁት ፕሮፌሰር በየነ፤ ይሁንና  ኃላፊነቱም ከእራሳቸው ራስ የሚወርድ አይደለም ብለዋል።
‘‘አቶ መለስ  ሹመት የምንሰጠው በአላማ ፅናት እንጂ  በችሎታ አይደለም እያሉ ምድረ-ሌባን ሲሾሙና ሲሸልሙ ኖረው ዛሬ ከ 21 ዓመታት ዝርፊያ በሁዋላ- የተሿሚዎቹ ሌብነት ታያቸው” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ተቃዋሚ ፓርቶዎች ስለ መልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ስለ ሙሰኝነት መባባስ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ዘረፋና ስለሌሎችም  በደሎች ከመጀመሪያው አንስቶ ሲናገሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።

“የሕዝቡን ሐብት እንደ ጠላት ንብረት ሲያዘርፉ እንደነበር ተናግረን ነበር’’ ያሉት ፕሮፌሰሩ፤” የሚያስገርመው ብዙ ሌቦች ይዘው ስለኢኮኖሚ እድገት ማውራታቸው ነው” ብለዋል።
ፕሮፌሰር በየነ አቶ መለስ መዋቅራቸው በሌቦች መጨማለቁን ቢገልፁም ፤ሌቦቹ  ስለ መቀጣታቸው አለመናገራቸው ሌላው ያስገረማቸው ጉዳይ መሆኑንም በመጥቀስ፤  “ነገሩ  ከልምድ እንዳነው፤የጠገበውን መዥገር አንስተው የራበውን መዥገር የመመደብ ስልት ነው’’ ማለታቸውን የሰንደቅ ዘገባ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 21 ዓመት ሙሉ ሀገሪቷን ሲያዘርፉ ከርመው ዛሬ ላይ ደርሰው ስለ ሌቦች ሲናገሩ፤ በሀገር ላይ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውንና ሲዘርፍ የነበረውን ቡድን ‘‘በአምበልነት’’ የመሩት እራሳቸው መሆናቸውን በመዘንጋት ፤በተሳከረ ቋንቋ ‘‘ሌባ’’ ብለው መግለፃቸው አስደናቂ እንደሆነባቸው ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

የሊዝ አዋጁን በተመለከተ ‘‘ሕዝቡን ስለናቁት ያወጡት አዋጅ ነው’’ ያሉት ፕሮፌሰሩ ‘‘በሌላ አገር ቢሆን ይሄ አዋጅ አገርን የሚያናውጥ፣ መንግስትን ከስልጣን የሚያስነሳና ማዕበል የሚቀሰቅስ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚመሩት መንግስት ቤሳቤስቲን የሌላቸውን ባለፎቅ ያደረገ መንግስት እንደሆነ የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ ‘‘‘ለምን ሚሊዮነር ትሉናላችሁ? ቢሊዮነር በሉን እንጂ! ሚሊዮን በብር ምን አላት? የሚሉ  ሰዎችን በአቋራጭ  እንዲናኙ ያደረገ ስርዓት እንደሆነ አብራርተዋል።
ፕሮፌሰር በየነ የሊዝ አዋጁ የወጣው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካድሬዎች ሕዝቡን ከዘረፉ ና  የራሳቸው ጥቂት ከበርቴዎች ቢሊዮነር ከሆኑ በኋላ እንደሆነ ያመለከቱት ፕሮፌሰር በየነ፤”  ከበርቴዎቹ ፎቅ ወደሰማይ ሰርተው ኪራይ እየሰበሰቡ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የሊዝ አዋጁ እነሱን አይቆነጥጣቸውም። የሚቆነጥጠው ጥቃቅን መሬት የያዘውን ዜጋ ነው “ብለዋል።
የአንድነት ፓርቲ የጽ/ቤት ጉዳይ ኃላፊ አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው የሊዝ አዋጁን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ሲያቀርቡ የነባር ይዞታ መሬት ካልተሸጠ በስተቀር ወደሊዝ አይገባም’’ ማለታቸው እና የታች ሹማምንቶቻቸው ደግሞ ነባር ይዞታ በጊዜ ገደብ ወደ ሊዝ ይገባል ማለታቸው፤ ኢህአዴጎች ተናበው እየሰሩ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሌላው የሊዝ አዋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልማት ጠቀሜታው ባሻገር የመንግስትንና የግል ሌቦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የደም ስራቸውን ለመዝጋት ነው ያሉት ከስድስት ጊዜያት በላይ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አስራት፤  በሌላ አገር ቢሆን እራሳቸው ለዚህ ተግባር ተጠያቂ ይሆኑ እንደነበር በቅርቡ በህንድ የሆነውን እንደምሳሌ በመጥቀስ አሳይተዋል -በህንድ አገር ባቡር ተገልብጦ ብዙ ሰዎች ከተጎዱ በኋላ ባቡሩን ያልነዳው የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ስልጣኑን እንደለቀቀ በማስታወስ።
‘‘የግል ሌቦቹ የመንግስት ሌቦች ባይኖሩ ኖሮ አይሰርቁም ነበር’’ ያሉት አቶ አስራት፤ የግል ሌቦችን የፈጠረና ያፋፋው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስተዳደር በመሆኑ ቢያንስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከስልጣን ባይወርዱ ሌቦቹን ቀጥተው ሊያሳዩ ይገባ ነበር ብለዋል።

መሬት እንደምክንያት ተነሳ እንጂ የአቶ መለስ ስርዓት በጠቅላላ በሙስና የተዘፈቀ መሆኑንም አቶ አስራት አያይዘው ገልፀዋል።
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሽብርተኝነት በላይ ሙስና ለአቶ መለስ መንግስት አደገኛ መሆኑ በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁ ትክክል መሆኑን የጠቀሱት አቶ አስራት እኛም በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት ስጋት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ስንገልፅ ቆይተናል ብለዋል።
መለስ  እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እዚህ ሀገር ተወልደው ያደጉና  ከሕዝቡም ጋር አብረው የኖሩ በመሆናቸው  የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሬት ላይ ያለውን ስሜት ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚል እምነት አለኝ “ያሉት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ይሁንና የሊዝ አዋጁ በዚህ ደረጃ ህዝቡን ያነጋግራል ብለው ገምተው እንዳልበር መግለፃቸው አስደንቆኛል ብለዋል።

አቶ መለስ “ይህን ሁሉ የሕዝብ ጫጫታ እና ውዥንብር አልተገነዘብነውም ማለታቸው፤ ተቀባይነት የሌለው የማምለጫ መንገድ ከመሆን አያልፍም’’ ሲሉም አቶ ሞሼ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ በአዋጁ ላይ  ከጠበቁት በላይ ተቃውሞ   እንዳሳየ   ቢጠቅሱም፤አዋጁ እንዲለወጥ እናደርጋለን ያሉበት ሁኔታ እንደሌለ የገለፁት አቶ ሞሼ፤ ይህም  ሕዝቡ የፈለገውን ያህል ቢቃወምም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አይን ተቃውሞው ሚዛን የሚደፋ አይመስልም ብለዋል።
የሊዝ አዋጁ የተቃዋሚ፣ የትምክተኛ እና የኪራይ ሰብሳቢ  ጉዳይ ሳይሆን በኢኮኖሚ ደረጃ ከትንሹ እስከ ትልቁ እያነጋገረ ያለና የሕዝብን ጥቅም የነካ በመሆኑ ተመልሶ ሊታይ የሚገባ እንደሆነም አቶ ሞሼ ጠቅሰው፣ ‘‘ሕግ ነፍስ ያለው ሕግ ለመሆን ፤የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልገዋል። ሕዝቡ የሊዝ አዋጁን የተገነዘበው፤ ሀብትን በመንጠቅ ዙሪያ ነው። ስለዚህ በጉልበት ሕጉን ማስፈፀም አይቻልም’’ ብለዋል።
ሙስናን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው በሌቦች መጨማለቁን ማመናቸው በበጎ ጎን የሚታይ  ቢሆንም፤ በሌቦቹ ላይ ምን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ግን አልነገሩንም ብለዋል።” ሌባ መኖሩ ማወቁ ብቻ በቂ አይደለም። እያወቁ ዝም ማለትም ሌቦቹን ይበልጥ ማበረታታት ነው” ሲሉም አክለዋል-አቶ ሙሼ።

አቶ መለስ መንግስታቸው ሙስናን በመዋጋት ደረጃ አበረታች ውጤት እንዳስመዘገበና ሙስና የሥርዓቱ አደጋ እንዳልሆነ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።