በትግራይ መለስን እንደ ቁምነገረኛ የሚቆጥረውና ንግግሩን የሚሰማ ሰው እየቀነሰ መምጣቱ ተነገረ

የካቲት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በትግራይ መለስ ዜናዊን እንደ ቁምነገረኛ የሚቆጥረውና ንግግሩን የሚሰማ ሰው እየቀነሰ መምጣቱን አቶ አስራት አብረሀ ተናገሩ

በተለያዩ ጽሁፋቸው የሚታወቁት የአረና ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብረሀ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ  ፣ “ድሮ የመለስን ንግግር ለመስማት የትግራይ ሰው ይጓጓ ነበር፣ መለስ ንግግር ካደረገ በሁዋላም አድናቆቱን ይገልጥ ነበር፣ በቅርቡ መለስ በፓርላማ ያደረገውን ንግግር ብዙ የመቀሌ ህዝብ ከጉዳይ አልቆጠረአልተከታተለውም ነበር፤ መለስን ነገሮችን ሸውዶ የሚያልፍ እንጅ ቁምነገረኛ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ቀንሷል፤ ህዝብ ስለመለስና ስርአቱ ያለው አመለካከት እየወረደ መምጣቱን አመላካችን ነው።” ብለዋል።

ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች ጥቅሙ እየተነካ ሲመጣ ለስርአቱና ለሰውየው ያለው አመለካከት እየወረደ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው የሚሉት አቶ አስራት፣ በአሁኑ ጊዜ የሚታዩት ምልክቶች ይህንኑ ያረጋግጣሉ ብለዋል።

አቶ አስራት ህወሀት የትግራይን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር ለማጋጨት ብቻ ሳይሆን የትግራይን ህዝብ እርስ በርስ ለማጋጨት እና ከፋፍሎ ለመግዛት ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ አቶ ስብሀት ነጋ የአክሱም ግዛት ሸዋን ይቅርና ተንቤንና አጋሜን አያጠቃልልም ብለው የተናገሩትን በዋቢነት አቅርበዋል

አቶ አስራት እንዳሉት በትግራይ ክልል ውስጥ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩት በአለቃ ጸጋየ ዘመዶች ተይዘው የነበሩት ቦታዎች በአዲሱ አስተዳዳሪ በአቶ አባይ ወልዱ ዘመዶች እየተያዙ መምጣታቸውን እና ሙስና በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱን ተናግረዋል።

ከኤትራ የሚነሱ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ በሚፈጥሩት ጥቃት ትግራይ የጦር ካምፕ እየሆነች መምጣቱንም አክለዋል።