የአዉሮፓ ህብረት ሁለቱ ስዊድናዉያን እንዲለቀቁ ጠንካራ ጫና በማድረግ ላይ ነው

የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ስዊድን አባል የሆነችበት አንድ የአዉሮፓ ህብረት የልኡካን ቡድን በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዉ ባለፈዉ መስከረም እስራት የተፈረደባቸዉን ሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞችን የአቶ መለስ መንግሰት እንዲለቅ ጠንካራ ዉይይት በማካሄድ ላይ እንዳለ ተገለፀ።

“ባለፉት ጥቂት ቀናት ከኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ጋር ስንነጋገር ነበር፡ ሁለቱ ጋዜጠኞች ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለን” በማለት ከጉዳዩ አሳሳቢነት የተነሳ ማንነታቸዉ እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የአዉሮፓ ህብረት ባለስልጣን ተናግረዋል። ባለስልጣኑ በማያያዝም “ ርዳታን ማቆም የመጨረሻ አማራጭ ነዉ” ብለዋል።
እኤአ ከ2008-2013 ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ህብረቱ 644 ሚሊዮን ይሮ ወይንም 838 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ የልማትና የሰብአዊ ርዳታ ማድረጉ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ከምእራቡ አለም በያመቱ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ከፍተኛ ርዳታ ተቀባይ አገር ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ምስራቅ አገሮች ማለትም ቻይናና ህንድ እንዳዘነበለች ሲታወቅ እስካሁን 650 ሚሊዮን ዶላር በብድርና በኢንቬስትሜንት ስም ማግኘቷን አፍሪካን ሪቪዉ የዜና ምንጭ ገልጿል።