ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለአፍሪቃዉያን ጥቅም የሚሰጥ ሳይሆን ይልቁንም ድሃ አነስተኛ ገበሬዎች የምግብ ዋስትና እንዲያጡና ከመኖሪያቸዉ እንዲፈናቀሉ የሚያደርገዉን የመሬት ቅርምትና ድርድር ከጀርባ ሆነዉ የሚያስፈፅሙት የአሜሪካን የልማት ድርጅት( USAID) ፣ የአለም ባንክና ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸዉን የገለፁት አሳሳቢ የፖሊሲ ጉዳዮችን በጥልቀት በማጥናት ለህዝብ በመቆም የሚሟገተዉ የኦክላንድ ኢንስቲትዩት መስራችና ዳይሬክተር አኑራ-ድሃ ሚታል ናቸዉ።
ዳይሬክተሯ ይህን የገለፁት ከታዋቂዉ የቺካጎ ህዝብ ሬድዮ ወርልድ ቪዉ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነዉ።
በመሬት ቅርምቱ ዉስጥ የሚገኙት ተቀራማቾች ምንም አይነት የእርሻ ልምድና ዕዉቀት እንደሌላቸዉና እኤአ በ2008 በአለም የምግብ ዋጋ መናር ላይ የተከሰተዉን ሁኔታ በመመልከት ትርፍ ለማግኘት ብቻ ተሳታፊ እንደሆኑ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል 70 ሺህ የሚሆኑ ደሃ አነስተኛ ገበሬዎችን ከይዞታቸዉ በሃይል በማፈናቀል መሬቱን ለዉጭ ኢንቬስተሮችና ባለሃብቶች ለመስጠት የሚደረገዉን ህገ ወጥ ተግባር አስመልክቶ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሒዩማን ራይትስ ዎች አንድ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሰዎች እራሳቸዉን ሊቀልቡ ወደማይችሉበት ቦታ በሃይል እንዲዛወሩ ማድረግ ስፋት ለሚኖረዉ ረሀብ የተዘጋጀ ከእዉነት የራቀ መደለያ እንደሆነ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሒዩማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ ላይ መጥቀሱ ይታወሳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዛኛው የጋምቤላ ህዝብ በክልሉ የሚካሄደውን የመሬት ነጠቃ እየተቃወመና እርምጃ መውሰድ እየጀመረ መምጣቱን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው በብዛት መስፈራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።