የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለኢህአዴግ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ዘመዶች መሰጠታቸው ቅሬታ አስነሳ

ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ልደታ አካባቢ የሚገኙ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለኢህአዴግ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ዘመዶች መሰጠታቸው ቅሬታ አስነሳ

በልደታ አካባቢ በመገንባት ላይ ያሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፣ ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ዘግይተው ቢጠናቀቁም ሰሞኑን እየተሰራ ያለው ድራማ ግን ህዝቡን ያሳዘነ ሆኗል።

የኢሳት ምንጮች እንዳሉት ኮንዶሚኒየም ቤቶቹ አስቀድመው ለገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና የባለስልጣናት ዘመዶች ተሰጥተዋል። የአካባቢው ነዋሪ ይህን ቢያውቅም፣ የመንግስትን ይፋዊ መልስ ለመስማት በመፈለግ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጥ ቆይቷል።

የአካባቢው ነዋሪ ማጉረምረም መጀመሩን ተከትሎ፣ የከተማዋ ባስልጣናት የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚሰሩት ቤቶች ጋር አንድ ላይ እጣ እንዲወጣላቸው ለማድረግ ዝግጅት መጀመራቸው ታውቋል።

ምንጮች እንደሚሉት ቤቶቹ እጣ እንዲወጣባቸው የሚደረገው ለማስመሰል ሲባል ነው እንጅ ፣ ድልደላው ከተፈጸመ ቆይቷል። እጣው የወጣላቸው ሰዎችም ስማቸው በጋዜጣ ይፋ ይሆናል ተብሎአል።

በርካታ የገዢው ፓርቲ ታማኝ ካድሬዎች ከአንድ በላይ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመያዝ እንደሚያከራዩ ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በፍጥነት ለማግኘት የገዢው ፓርቲ አባል መሆን ግድ ይላል ይላሉ ምንጮች።