የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ያሏቸዉን በቁጥጥር ስር አዋሉ

ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች  ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ያሏቸዉን አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋሉ

በሶማሊያ ሂራን ክልል በበለደ-ወይን ከተማ የኢትዮጵያ ወታደሮች  ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳላቸዉና በወታደራዊ ካምፖች ላይ የሽብር ጥቃት ሊፈፅሙ ነበር ያላቸዉን አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ነዋሪዎች ገለጸዋል።

ባለፈዉ እሁድ ጥዋት በከተማዉ ዉስጥ በተወሰደዉ እርምጃ በቁጥጥር ስር የዋሉት አምስት ግለሰቦች በቅርቡ በከተማዉ ዉስጥ የደረሰዉን የቦንብ ፍንዳታ ያቀዱና የፈፀሙ ናቸዉ በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች እንደወነጀሏቸዉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ጦር  የከተማዋን መዉጫና መግቢያ መንገዶች በመዝጋት በወሰደዉ እርምጃ  በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከቀናት በፊት በከተማዋ ዉስጥ ተፈጥሮ ስለነበረዉ የፀጥታ ችግር ሊጠየቁ እንደሚችሉ ታዉቋል።

በቅርቡ አልሸባብ በኢትዮጵያ ወታደሮች ካምፕ ላይ በሰነዘረው ጥቃት ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።