ጥር 26 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በ2000 ዓም ለተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት ተብሎ በተቋቋመው የፓርቲዎች የምክክር ምክር ቤት ታቅፈው በገዥው ፓርተ በተረቀቀው የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ላይ ከመከሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል፤ በአቶ ልደቱ አያሌው የሚመራው ኢዴፓና በኢንጂነር ሀይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ ዋነኞቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፤ ምክር ቤቱ የተዋቀረበትን ሂደት በመቃወሙና አደረጃጀቱ እንዲሻሻል በመጠየቁ ሳቢያ በኢህአዴግ ከመገፋቱም ባሻገር፤ ገዥው ፓርቲ ከነመኢአድና ኢዴፓ ጋር የደረሰበት የስምምነት ሰነድ ላይ፦ “አልፈርምም” በማለቱ፤ በአመራሮቹ ላይ የዛቻና የማስፈራሪያ ዘመቻ ተከፍቶባቸው መሰንበቱ ይታወሳል።
በኢህአዴግ አርቃቂነት ፓርቲዎቹ ተወያይተው ባፀደቁት ሰነድ ላይም፤ገዥውን ፓርቲ ወክለው አቶ መለስ ዜናዊ፣ኢዴፓን በመወከል አቶ ልደቱ አይሌው እና መኢአድን በመወከል ኢንጂነር ሀይሉ ሻውል ፊርማቸውን አኖሩ።
በሸራተን አዲስ በተካሄደው በዚሁ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ በተለይ አቶ መለስና ኢንጂነር ሀይሉ ሲጨባበጡ መታየታቸው ፤የበርካታ መገናኛ ብዙሀንን ቀልብ ሳበ።
በርካታ የመኢአድ አባላት ግን ዕለቱን፤የፓርቲያቸው የውድቀት ቀን እንደሆነ አድርገው በቁጭት ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ከፊርማው ስነ ሥርዓት በሁዋላ ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል ባደረጉት ንግግር ፦”ዲሞክራሲያዊ የሆነ ደንብ አጽድቀናል።ከደንቡ ውጪ የሚሰሩ ካድሬዎች ካሉ፤ እየተመካከርን ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ተስማምተናል። ከእንግዲህ የጫጫታ ፖለቲካ ቦታ የለውም።ጩኸት በማብዛት የሚለወጥ ነገር አላየንም።በመመካከር ግን ወደፊት መጓዝ እንችላለን። ስንጠይቀው የነበረውን ነገር አግኝተናል”ማለታቸው አይዘነጋም።
ያን ደንብ ተከትሎ በተከናወነው አገር አቀፍ ምርጫ ፤ኢህአዴግ ሁሉንም የተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ጠቅልሎ ያዘ።
በምርጫው ኢፍትሀዊነት ዙሪያ መኢአድን ጨምሮ ከበርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ጎረፉ። ሆኖም ግን አንዳቸውንም እንኳ በተፈረመው ደንብ መሰረት ለማጣራትና የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ፤ከኢህአዴግ በኩል ፈቃደኝነቱ ጠፋ።
ገዥው ፓርቲ 99 ነጥብ 6 በመቶ በሆነ ውጤት ምርጫውን ማሸነፉን በገሀድ አወጀ።
አርቲስት ታማኝ በየነ በቅርቡ በ አንድ መድረክ ላይ ገለፃ ሢሰጥ፦” 99 ነጥብ 6፤ የምርጫ ውጤት ነው? ወይስ በዲግሪ ፋራናይት የተቀመጠ የሰውነት “ቴምፕሬቸር”መጠን?”በማለት መጠየቁ ይታወሳል:፡
የቀረችው አንዲት ወንበርም-በስነ ምግባር ደንቡ ያልፈረመው የመድረክ ነች። ተስፋ ሰንቀው ወደ ምርጫው የገቡት የአቶ ልደቱ ኢዴፓና የኢንጂነር ሀይሉ መኢአድ ፤ ባዷቸውን ቀሩ።
ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ወዲያውኑ የፓርቲዎቹ ምክር ቤት ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደረገ።
ብዙም ሳይቆይ መኢአድ በውስጥ ልዩነት መታመስ ጀመረ። ከዛሬ ነገ እልባት ያገኝ ይሆናል የተባለው ውስጣዊ ችግር እየተባባሰና እየሰፋ መጣ። በዚህ መሀከል የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በተለየ መልኩ የመኢአድ አባላትን እያሳደዱ መምታት ጀመሩ።በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ በፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ፤ አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደረሰ።
የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሪት መሶበወርቅ ቅጣው እንዳሉት፤ከሳምንት በፊት ብቻ በደቡብ ክልል 38 የመኢአድ አባላት ታስረዋል።
እንዲሁም በዳሰነች ምርጫ ክልል ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው የነበሩት ወ/ሮ አማረች ገላኔ በ23
ጥይት ተደብድበው እንደተገደሉና የ10 እና 12 ዓመት ህፃናት ልጆቻቸው በጥይት እንደቆሰሉ ፤ ባለቤታቸው አቶ ጌልሄሎ ኩይታ ደግሞ ሀዘናቸውን በመግለፃቸው ብቻ ስለት በያዙ ሰዎች ማስፈራሪያ እንደተፈፀመባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።
“የጩኸት ፖለቲካ ቦታ ያለውም” ያለው መኢአድ፤በተለየ መልኩ ባለፉት ወራት በአባሎቹ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስመልክቶ ተከታታይ አቤቱታዎችን በማሰማት ላይ ይገኛል።
የምርጫ 2002ን መጠናቀቅ ተከትሎ ስራውን እንዲያቋርጥ የተደረገው የፖርቲዎች ምክር ቤት በኋላ ላይ የቀጠለውም ፤ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች በደንብና መመሪያዎቹ ላይ እንደገና ከተለያዩ በኋላ መሆኑን የምክር ቤቱ ምንጮች ገልፀዋል።
እንደ ቪኦኤ ዘገባ፤ ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል፤ ከአሥር ያላነሱ መደበኛ ስብሰባዎችን አድርጓል።
በዚህ መሃል ነው- የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ራሡን ያገለለው።የፓርቲው ፕሬዚደንት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል፤ድርጅታቸው ከምክር ቤቱና ከገዥው ፓርቲ ጋር የፈጠው ልዩነት ሊፈታ እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ከዚህም በላይ መኢአድ የምክር ቤቱን አሠራር ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ስላላገኘው፤ ከምክር ቤት አባልነቱ ራሱን ማግለሉን አስታውቀዋል።
ከአዲስ አበባ የሚወጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት፤ መኢአድ የወሰደው ከምክር ቤቱ ራሱን የማግለል እርምጃ፤ በብዙሀኑ የፓርቲው አባላት ዘንድ ከፍ ያለ ድጋፍ አስገኝቶለታል። እርምጃው ከዚህም ባሻገር በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት በመፍታት ረገድ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ በኩል ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።