የመንግስትና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ፍጥጫ ቀጥሎአል

ጥር 25 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለመንግስት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጣቸው ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

በዛሬው እለት የአርብን ጸሎት ምክንያት በማድረግ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአወልያ መስጊድ ተገኝተው እንደነበር በስፍራው የተገኘው ዘጋቢያችን ገልጧል።

ሙስሊሞቹ ከዚህ ቀደም ላቀረቡት የመብት ጥያቄ የመንግስትን መልስ ከተወካዮቻቸው ለመስማት በብዛት ቢገኙም፣ የጠበቁትን መልስ ለማግኘት አልቻሉም።

የሙስሊሞቹ ተወካዮች ከመንግስት ጋር ተከታታይ ውይይት ለማድረግ በሚቀጥለው ሳምንት  ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ገልጠዋል።

ምንም እንኳ በርካታ ሙስሊሞች መንግስት ችግሩን ለለመፍታት መፈለጉን፣ እንዲሁም እንቅስቃሴውን ለማፈን ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢያምኑም፣ እስከ መጨረሻው ድረስ ተወካዮቻቸው የሚያቀርቡትን አማራጭ ለመቀበል በመወሰን ተለያይተዋል።

ሙስሊሞቹ የእስልምና ምክር ቤት ወይም መጅሊስ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር፣ መንግስት የአህባሽን አስተምህሮ ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም፣ የአወልያ ኮሌጅ እንዲከፈት ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

መጅሊሱ ግን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄው ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳለው በመግለጥ ወደ አልተፈለገ ግጭት እንዲያመራ እየጋበዘ መሆኑን ሙስሊሞች ለኢሳት ዘጋቢ ገልጠዋል።

1 ሺ 486ኛውን የነብዩ ሙሀመድን የመውሊድ በዓል ምክንያት በማድረግ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼክ አህመዲን አብዱላሂ በሰጡት መግለጫ ሙስሊሙ በሀይማኖት ሽፋን የሚደረጉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ማውገዝ አለበት ብለዋል።

የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት እንዳሉት የግልና የቡድን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሙስሊሙን ለመከፋፋል፣ ሰላማዊ ኑሮውን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች አሉ።

ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን በመላው አገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻም አውግዘዋል።

ጥር 26 በሚከበረው የመውሊድ በአል ላይ የጸጥታ መደፍረስ ይነሳል በሚል ፍርሀት መንግስት ከፍተኛ የጥበቃ ስራ እየሰራ መሆኑን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን ገልጦአል።

ከቅርብ ሳምንታት በፊት በአወልያ የታየው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ፣ ምናልባትም በነገው እለት በስታዲየም በአል አከባባር ላይ ጎልቶ ሊታይ ይችላል የሚል ግምት መኖሩን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።