የኤድስ ፈንድ ለፖለቲካ ድጋፍ መሸመቻ እየዋለ ነው

ጥር 26 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለኤዲስ መከላከያ ተብሎ ከመንግስታት የሚለገሰው ገንዘብ ፣ ኢህአዴግ ለፖለቲካ ጥቅም ማስገኛ እያዋለው መሆኑን የቀድሞው የተስፋጎህ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ተናገሩ።

ተስፋ ጎህን ለረጅም አመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ታደሰ አይናለም ለኢሳት እንደተናገሩት በኤች አይቪ ቫይረስ ለተጠቁት ወገኖች ተብሎ ከግልኦባል ፈንድ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከተለያዩ በርካታ አለማቀፍ ድርጅቶች የሚለገሰው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣ በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ትእዛዝ ብቻ ከታለመለት አላማ ውጭ እንዲውል ይደረጋል።

አቶ ታደሰ እንደሚሉት ገንዘቡ ለሬዲዮ ፋናና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በማስታወቂያ ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲፈስ ይደረጋል። ሬዲዮ ፋና በአዲስ አበባ ውስጥ የገነባው ዘመናዊ ህንጻ ገንዘብ አብዛኛው ምንጭ የኤድስ ፈንድ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ መንገዶች ለእርዳታ ተብሎ የሚሰጠውን ገንዘብ ለፖለቲካ ድጋፍ ማስገኛ እንደሚያውለው ሂውማን ራይትስ ወች መግለጡ ይታወሳል።