ጥር 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ወታደራዊ መግለጫ እንደማለከተው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በየወቅቱ የሚያደርጉትን ህዝቡን የማስፈራራትና ማዋከብ ዘመቻ ጀምረዋል።
በዋርዴር ቀብሪ ደሀርና ደገሀቡር አካባቢዎች የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የአካባቢውን እያመሰነ ነው ሲል ገልጧል።
ግንባሩ ሂጋን በተባለው አካባቢ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ባደረገው የተኩስ ልውጥጥ 50 ገድሎ 70 ማቁሰሉን ገልጧል። 5 ቢኬኤም ከባድ ጠመንጃዎችን፣ 40 የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከወታደሮች ላይ ማስጣሉን ገልጧል።
በደገሀቡርና ቀብሪ ደሀር አካባቢዎች በተመሳሳይ ቀን በተፈጸመ ጥቃት 4 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን አውድሟል። በዚሁ ጥቃት 60 የመንግስቱ ወታደሮች መገደላቸውን የግንባሩ ወታደራዊ ክፍል ገልጧል።
ኦብነግ በራሱ ሰራዊት ላይ ስለደረሰው ጉዳት አነስተኛ ከማለት ውጭ የገለጠው ነገር የለም።
ስለተገደሉት ወታደሮችም ሆነ ስለወደመው ንብረት የኢትዮጵያ መንግስት ማስተባበያ አልሰጠም፣ አካባቢው ለጋዜጠኞች ዝግ በመሆኑም በገለልተኛ ወገኖች ለማጣራት አይቻልም።
ይሁን እንጅ ግንባሩ መንግስት በደረሰበት ጉዳት በመበሳጨት በሚቀጥሉት ተከታታይ ሳምንታት በአካባቢው አዲስ የጥቃት ዘመቻ ሊከፍት ይችላል ብሎአል።