በአለፈው አመት ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ይልቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ተሰደዋል

ጥር 12 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-መንግስት አልባዋ ሶማሊያ ለአለፉት 10 አመታት ስደተኞችን በማምረት በኩል የሚስተካካላት አልነበረም፡ አሁን ግን ይህን ሪኮርድ ኢትዮጵያ ውስዳለች። ረዩተር ባወጣው ዘገባ በአሳለፍነው የፈረንጆች አመት በሪከርድነት የተመዘገበ 103 ሺ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን በሰላም እጦት አደጋ ውስጥ ወዳለችው የመን አቀንተዋል።

ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ከአራቱ እጅ ሶስቱ ወይም ከ77 ሺ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊ  ቀሪዎቹ 25 ሺ ደግሞ ሶማሊያውያን ናቸው።ባለፈው አመት ብቻ 130 ስደተኞች የመን ባህር ውስጥ ሰምጠው ሲቀሩ፣ በጣም በርካቶች ደግሞ በደላሎች ተገድለዋል።

ወደ የመን የሚገቡት ስደተኞች፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ፣ የጠወለጉ እና ባሳለፉት ህይወት የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ችግር ያለባቸው ናቸው። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ስደተኞች ህይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ የሚሰደዱ ናቸው። የ የመን የህዝብ አመጽ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር ቢኖርም፣ ኢትዮጵያውያንን ከስደት አልገታቸውም።

ረዩተር እንደሚለው የኢትዮጵያን ስደተኞች ሁኔታ የከፋ የሚያደርገው አብዛኞቹ ስደተኞች እንደምንም ብለው ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሉ ሩቅ ከሆነው የአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች እየፈለሱ የመጡ መሆናቸው ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ስራ አጥነት፣ ረሀብና የፍትህ እጦት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አገራቸውን ጥለው በገፍ እንዲሰደዱ እንደሚያደርጋቸው ጥናቶች ያመለክታሉ።

ከአመት በፊት የወጣ ጥናት ኢትዮጵያውያን እድሉን ቢያገኙ ከ46 በመቶ በላይ የሚሆኑት አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ በማለት መዘገቡ ይታወሳል።

የኤደንን የባህር ሰላጤ አቋርጠው የሚወጡት ስደተኞች ቁጥር፣ በኬንያ እና በሱዳን በኩል እያቋረጡ ከሚወጡ ስደተኞች ቁጥር  ጋር ሲተያይ አነስተኛ መሆኑንም የዩኒኤች ሲአርና አይኦኤም መረጃዎች ያሳያሉ።