ጥር 11 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በማእከላዊ ሶማሊያ ባላዲወይኒ ሂራን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ባሳፈረ ተሽከርካሪ ላይ በቅርብ ርቀት መቆጣጠሪያ / ሪሞት ኮንትሮል/ የተቀሰቀሰ የቦንብ ፍንዳታ መድረሱን ሸበሌ ሚዲያ ኔት ወርክ የዜና ወኪል ገለጸ።
በተሽከርካሪዉ ላይ በተጫኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ የተገለፀ ሲሆን ፍንዳታዉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአካባቢዉ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎችን ሲገድሉ አምስት ሰዎችን ማቁሰላቸዉን የአይን ምስክሮች መናገራቸዉን የዜና ምንጩ አመልክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሰት ወታደሮች በጥቃቱ የተጠረጠሩ አስር ሰዎችን ሰብስቦ ማሰሩ ተገልጿል። በተኩሱ የቆሰሉት ሰዎች በባላዲወይኒ ሆስፒታል በህክምና ላይ ሲገኙ እስካሁን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ አካል አለመኖሩን ለመረዳት ተችሏል።