ኢትዮጵያዊዉ ቤተ እስራኤላዊ ባለቤቱን በስለት ገድሎ እራሱን ሰቅሎ አጠፋ

ጥር 11 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-ላዋካ አማራ የተባለዉ የ37 አመት ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዊ የ32 አመት እድሜ ያላትን የሶስት ልጆቹን ወላጅ እናት በስለት ወግቶ በመግደል እራሱን ሰቅሎ እንዳጠፋ ሃሬትዝ የዜና ምንጭ ገለጿል።

ከአምስት አመት በፊት ወደ እስራኤል የተጓዙት ሁለቱ የትዳር ጓደኞች በአንድ ትልቅ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ዉስጥ የሚሰሩ ሲሆን ለዚህ መጠፋፋት የደረሱበት የግጭት መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን አልተገለፀም።

እድሜያቸዉ 10፤ 12 እና 5 የሆኑት 3 ልጆቻቸዉ ከአደጋዉ በሁዋላ በአካባቢዉ ዘመድ ዘንድ እንዲሰነብቱ የተደረገ ሲሆን ከደረሰባቸዉ መጥፎ አደጋ ከተረጋጉ በሁዋላ ለወደፊቱ የተሻለ መፍትሄ እንደሚፈለግላቸዉ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያዉያን ቤተእስራኤላዊያን ዘንድ በየጊዜዉ ይህን መሰሉ የግድያ ወንጀል መፈፀሙ የተለመደ መሆኑ ያሳሰበዉ የእስራኤል የኢሚግሬሽን ሚኒስቴር መ/ቤት ሁኔታዉን በባለሙያ ማስጠናቱ ታዉቋል። 

ይሁን እንጂ በ2009 የተጠናቀቀዉ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የጥናት ዉጤት የግለሰቦችን መብት የሚነኩ በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች የተካተቱበት በመሆኑ ጥናቱን ሙሉ በሙሉ ለህዝብ ለመግለፅ ፈቃደኛ እንዳልሆነ የዜና ምንጩ አስታዉቋል።

በኢትዮጵያዊያን ቤተእስራኤላዉያን ላይ ከ30 አመት ላላነሰ ጊዜ ምርምር ማድረጋቸዉ በሚነገርላቸዉ የአንትሮፖሎጂ ምሁር ዶር ሻልቫ ዌይል በተደረገዉ ጥናት በእስራኤል በሴቶች ላይ ከሚፈጸመዉ ግድያ 28.2% የሚደርሰዉ  ኢትዮጵያዊ/ቤተእስራኤላዊያን መሆኑ፡

ግድያዉን ከሚፈፅሙት 81 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሌላቸዉ መሆኑ፡ከግማሽ የማያንሱት ገዳዮች ስራ የሌላቸዉና ከሟቾቹ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቤት እመቤቶች መሆናቸዉ ተጠቅሷል።