በሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸዉ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ጥፋተኛ መባላቸውን የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች እያወገዙት ነው

ጥር 11 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-በነኤልያስ ክፍሌ  የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ተጠርጥረው በታሰሩት 3 ጋዜጠኞች ፣ ሁለት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባልና ደጋፊ  ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ትናንት የጥፋነተኝነት ብይን መስጠቱ ይታወሳል ።

በሌለበት ብይኑ የተላለፈበትን የEthiopian Review ድረ ገፅ ዋና አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌን ጨምሮ፤ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዕዮት ዓለሙ፤ በቅርቡ ከህትመት የወጣዉ የሳምንታዊው አውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪና ደጋፊ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሄርና ሂሩት ክፍሌ የመጨረሻውን ውሳኔ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰማሉ።

አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት የአፍሪካ ወኪል የሆኑት ሙሀመድ ኬታ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን እርምጃ አውግዘዋል

ጋዜጠኞቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው ተወካዩ ይናገራሉ።

ሲፒጄ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መነጋገሩን የገለጡት ሙሀመድ ኬታ ፣ መንግስት ግን አሁንም ጋዜጠኞቹ ጥፋተኛ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል“ በንግግር ነፃነት ላይ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ስድብና ጀብደኝነት“   በሚል ባወጣዉ መግለጫ 5 ቱ ተከሳሾች የህሊና እስረኞች መሆናቸውን ገልጾ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይኖራል ብሎ እንደማያምን በማስታወቅ የፍርድ ቤቱ ብይን አጣጥሎታል ።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተመራማሪ ክሌይር ቤስተን “ በተከሳሾቹ ላይ የቀረቡት አብዛኛዎቹ የክስ ማስረጃዎች በመንግስት ላይ ሰላማዊ ተቃዉሞ ለማካሄድ የተደረጉ ጥሪዎች ናቸዉ። ሌሎች ማስረጃዎች ደግሞ ተከሳሾቹ የጻፏቸዉ ፅሁፎችና ሌሎች ግለሰቦች የላኩላቸዉ ናቸዉ።  ይህ የሚገልፀዉ  ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በችሎቱ ላይ እንደተወነጀለና በመንግሰት ላይ ትችት ማቅረብ ወንጀል መሆኑን ነዉ። ብይኑ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ሰዎች፤ የተለየ ሃሳብ ያላቸዉ ግለሰቦች፡ወይም በፖለቲካዉ ሂደት ላይ ገለልተኛ የሆነ ትችት ለመሰንዘር የሚሞክሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ዉስጥ ስፍራ እንደሌላቸዉ ያመለክታል።” ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣዉ በዚሁ መግለጫ አምስቱ የህሊና እስረኞች የተከሰሱት ህጋዊና ሰላማዊ የሆነ ተግባራቸዉን በማከናወናቸዉ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል በማለት ጠይቋል።

ሒዩማን ራይትስ ዎች ከናይሮቡ ብይኑን በማስመልከት “የንግግር ነፃነትን መጨፍለቅ” በሚል ርእስ ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሰት ክሱን ዉድቅ አድርጎ፤ ተከሳሾቹን ፈትቶ፤ በእስር ቤት ስለደረሰባቸዉ ግርፋትና ሰቆቃ ያቀረቡትን አቤቱታ እንዲያጣራ መጠየቁ ይታወሳል።

መንግስት የሚቃወሙትን ሁሉ ሽብርተኛ የሚል ስያሜ በመስጠት ዝም ለማሰኘት ይፈልጋል በማለት የሲፒጄ የአፍሪካ ወኪል የሆኑት ሙሀመድ ኬታ ተናግረዋል።

ትናንት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፍርዱን በንባብ በሚያሰማበት ጊዜ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ፍርድ የእግዚሃብሄር ነው የሚል ጽሑፍ በአጀንዳው ላይ አስፍሮ ለጋዜጠኞች አመላክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፍርድ ሃሳቡን በንባብ ካሰማ በኋላ ከዐቃቤ- ሕግና ከተከሳሽ ጠበቆች የቅጣት አስተያየት የተቀበለ ሲሆን የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ተከሳሦቹ የፈጸሙት ወንጀል በሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሽፋንና በጋዜጠኝነት ሥም ከአሸባሪ ቡድን ጋር በመደራጀት፣ የአድማ ስምምነት በማድረግ፣ አመራርና አባል ሆነው ሁከት ለመፍጠር፣ በ2004 ዓ.ም የመንግስትን መሠረተ- ልማቶች ለማውደምና ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ በመሆኑ ወንጀሉም ደረጃ ያልወጣለት በመሆኑ በከባድ ቅጣት እንዲያዝልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ተፈጸመ የተባለው ወንጀል በሕግ የተፈቀዱ ተግባሮችን ለማህበራዊ ለውጥ ለማከናወን ሲባል መሆኑን፣ ተከሳሾች የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ ጋዜጠኛ በመሆን ሥራቸውን ሲያከናውኑ ሕግ ያለፉ እንጂ በአፍቅሮተ ንዋይና በወራዳነት ተግባር ያደረጉት እና ወንጀሉም ያልተተገበረ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት በዝቅተኝነት ደረጃ እንዲመለከተውና እነዚህ ተከሳሾች የቤተሰብ ኃላፊዎች በመሆናቸው ከሚታሰሩ በገደብ አሊያም በገንዘብ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱን እንለምናለን ብለዋል፡፡

በመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ፣ ቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና ግራ ዳኛ በሪሁን አራጋው ግራ ቀኝ ተነጋግረው ፍር ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በ4ተኛ ተከሳሽ ላይ በማክበጃነት የጠቀሰውን ከዚህ ቀደም በግንቦት ሰባት አባልነት ተሳትፈው በሁለት ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ በጽቤት በኩል እንዲያቀርብ፣ የተከላካይ ጠበቆችም ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ እንዲሁ እንዲያቀርቡ በማዘዝ ለፍርድ ለጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ከሰሃት በኋላ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡