(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 12/2011)ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተዘረፈ ከ1ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዶላር ጋር በተያያዘ አንድ ናይጄሪያዊ ባለሀብት መታሰራቸው ተገለጸ።
የሲንጋፖር ፍርድ ቤት ባለፈው ሃሙስ ባዋለው ችሎት ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ያላቸውና በሲንጋፖር የሚኖሩት ናይጄሪያዊ ባለሀብት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዲሸሽ አድርገዋል በሚል ክስ የሶስት ዓመት እስር በይኖባቸዋል።
ገንዘቡን በተለያዩ የብሔራዊ ባንክ ሃላፊዎች ፍቃድ በመውሰድ ለናይጄራዊው ባለሀብት ሲያስተላለፉ ነበሩ የተባሉት ጓደኛቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ መሆናቸው ታውቋል።
ለናይጄሪያዊው ጓደኛ ናቸው በተባሉት በኚህ ግለሰብ ገንዘቡ ይተላለፍ እንደነበር ሲንጋፖር ቱዴይ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ባለፈው ሀሙስ የተሰየመው የሲንጋፖር ፍርድ ቤት ከ2008 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጀምሮ የነበረውንና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተወሰደውን ገንዘብ ጉዳይ ተመልክቶ ብይን ሰጥቷል ይላል የሲንጋፖር ጋዜጣ።
ከ27 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጪ ተደርጎ ኒዮርክ በሚገኝ ሲቲ ባንክ ውስጥ አካውን ተከፍቶ ተቀምጧል ያለው ፍርድ ቤቱ ከዚህ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ያለውን ናይጄሪያዊ ባለሀብት በሶስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን መረጃው ያመለክታል።
በክሱ መዝገብ ላይ እንደተገለጸው በ2008 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሁለት ሳምንት ውስጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተጻፈና የ24 ክፍያዎች እንዲፈጸሙ የሚጠይቅ ደብዳቤ ላይ በተለያዩ ሃገራት ለሚገኙ አካላት ገንዘብ እንዲተላለፍ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ገንዘቡን ኢትዮጵያ ከሚገኝና ከመንግስት ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች አብሮ እንደሚሰራ በሚገልጽ ግለሰብ አማካኝነት በማውጣት ሲንጋፖር ያሉ በትውልድ ናይጄሪያዊ በሆኑ ባለሀብት በከፈቱት የኒውዮርክ ሲቲ ባንክ አካውንት እንዲገባ መደረጉን ነው በክሱ ላይ የተገለጸው።
ናይጄሪያዊው ባለሀብት ኢትዮጵያ ካለው ወዳጃቸው የሚላክላቸውን በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር በሲንጋፖር ማስቀመጥ አደጋ አለው በሚል ኒውዮርክ ወዳለው ሲቲ ባንክ አካውንት በመክፈት ማስቀመጣቸውም ተመልክቷል።
ገንዘቡ በተለያየ መጠን ከሲቲ ባንክ ደግሞ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንዲተላለፍ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
ናይጄሪያዊው ባለሀብት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፕሮጀክቶች ስም ከሚሸሸው ገንዘብ በኮሚሽን እንደሚያገኙ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል ከ27ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎ ከሀገር እንዲወጣ ፍቃድ የሰጡ ሃላፊዎች እነማን እንደሆኑ በዘገባው ላይ አልተገለጸም።
ኢሳት ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ብሔራዊ ባንክ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የባንኩ አንድ ሃላፊ ለኢሳት እንደገለጹት ጉዳዩ በህግ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ በማሸሽ እጃቸው ያለበት አንድ የባንኩ ከፍተኛ ሃላፊ በመቀሌ ተደብቀው እንደሚገኙ ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።