የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሻሻል ውሳኔ ተሰጠ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 12/2001) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸረ ሽብር ህጉ በዜጎች መብትና ነጻነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው በማለት እንዲሻሻል ውሳኔ ሰጠ።

ባለፈው ቅዳሜ የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2001 የጸደቀው የጸረ ሽብር ህግ የይዘትና የአፈጻጸም ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ እንዲሻሻል ውሳኔ አቅርቧል።

ህጉ የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ ረቂቅ አዋጅ እንዲሻሻል ምክር ቤቱ ወስኖ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ምርጫ 97ትን ተከትሎ በህወሃት አገዛዝ ከወጡ አምስት አፋኝ ናቸው የተባሉ ህጎች አንዱ ላይ ነው ባለፈው ቅዳሜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያስተላለፈው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ላይ እንደተመለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸረ ሽብር ህጉን በዜጎች መብትና ነጻነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ብሎታል።

በይዘትም ሆነ በአፈጻጸም ክፍተቶች ያሉበት ህግ ነው ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህጉ እንዲሻሻል ከውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም፣ በተረጋጋና በነጻነት እንዲኖር ለማድረግ ነው በሚል የተቀረጸውና ጸድቆ አያሌ የፖለቲካና የመብት ተሟጋቾችን ለእስራት የዳረገው የጸረ ሽብር ህጉ ዓለም ዓቀፍ ውግዘት ሲደርስበት ቆይቷል።

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና የተለያዩ ሃገራት ህጉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ከመጨፍለቅ አንስቶ የኢትዮጵያ ህዝብን በአፈና ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግ ነው በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ ቢቆዩም የህወሃት አገዛዝ ሳይቀበለው ቀርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን በያዙ ዕለት ይህን ህግ ጨምሮ ሌሎች አፋኝ የሆኑ አዋጆችን እንደሚከልሱት ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው።

ብዙዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አካሄድ የጸረሽብር ህጉና ሌሎች አዋጆችን በፍጥነት በማስወገድ ለስር ነቀል ማሻሻያ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ይሆናሉ ብለው ጠብቀው ነበር። ሆኖም ህጎቹ እስካሁን ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ቆይተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዓለም ዓቀፍ ውግዘት በገጠመውና ኢትዮጵያውያንን ለአፈና በዳረገው የጸረ ሽብር ህጉ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ የጸረ ሽብር ህግ መኖሩ ጠቀሜታውን በመግለጽ በፊት የነበረው ህግ ግን የዜጎችን ነጻነት የሚጋፋ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል ብሏል።

በዚህም መሰረት በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተዘጋጀውና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አገናዝቧል የተባለውን ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዝርዝር ተወያይቶ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

የተሻሻለው የጸረ ሽብር ህጉ ዝርዝር ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

ከጸረ ሽብር ህጉ በተጨማሪ የበጎ አድርጎት ማህበራት፣ የፕሬስና የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጆችም በህወሃት አገዛዝ የጸደቁና ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመራር ህጎቹን ለማሻሻል ቃል መግባቱ የሚታወስ ነው።