በምዕራብ ጉጂ ሰባት ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14/2011)በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

በምዕራብ ጉጂ ልዩ ስሙ ደራራ በሚባል አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉት ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ፋይል

ባለፈው ሳምንትም ሀረቀሎ በተባለ ቦታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ጥቃቱን የኦነግ አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች መከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ የመንግስት ወታደሮች በወሰዱት ርምጃ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ጥቃቱ በየጊዜው የሚደርስ በመሆኑ ህዝቡ ተረጋግቶ መኖር አልቻለም ሲሉም ገልጸዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመከላከያ ሰራዊት አልተወሰደም ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የተከሰተውን ግድያ በተመለከተ የተለያዩ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት እንደሆኑ በሚገልጿቸው ታጣቂዎች በሚደረግ ጥቃት ምክንያት የመከላከያ ሰራዊት በንጹሃን ላይ ግድያ እየፈጸመ ነው ይላሉ።

ቢቢሲ አማርኛ ከትላንት በስቲያ ጎሮ ዶላ ወረዳ ውስጥ አስር ሰዎች ተገድለው መገኘታቸውን የአካባቢውን አንድ ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።

የኦነግ ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል መገደሉን ተከትሎ በተወሰደ ርምጃ 10 ሰዎች መገደላቸውን ነው የቢቢሲ አማርኛ ዘገባ የሚያመለክተው።

ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ ግን በጉጂ ዞን ደራራ በተባለ ቦታ ስለተፈጸመው ግድያ ይናገራሉ።

ከአምስት እስከ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል ነው የሚሉት ነዋሪው።

በጉጂ ዞን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እየተደጋገመ እንደመጣ የሚገልጹት ነዋሪዎች በታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት አማካኝነት የሚደረገው ግጭት መጨረሻው የሰላማዊ ዜጎችን ሞት እያስከተለ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንትም ተመሳሳይ ግድያ መፈጸሙን ነው ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪ የሚገልጹት።

መንግስት የኦነግ ሰራዊት ትጥቅ ፈቶ ወደካምፕ እንዲገባ ተደርጓል ይላል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ አመራሩ በእኔ የሚታዘዝ ሰራዊት የለኝም ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው።

በተደጋጋሚ በኦነግ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶችንም ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።

በእርግጥ በጉጂ ዞን ጥቃት አድርሰዋል የተባሉት የኦነግ ታጣቂዎች ስለመሆናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከሚሰጡት ምስክርነት ባለፈ በሌላ ወገን ማረጋገጫ አልተገኘም።

ለቢቢሲ አማርኛ መረጃ የሰጡ የአካባቢው ባለስልጣን እኛም ከህዝቡ የሰማነው የኦነግ ታጣቂዎች መሆናቸውን ነው በማለት ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በኦነግና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በሚደረግ ግጭት በመሃል ሰላማዊ ዜጎች እየተጎዱ ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለቱም ወገኖች ለህዝብ እያሰቡ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ቢቢሲ አማርኛ ያነጋገራቸው የአካባቢው ባለስልጣን በኦነግና በመከላከያ ሰራዊት መሀል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ህይወቱ ያለፈ ሰላማዊ ዜጋ ሊኖር እንደሚችል አልሸሸጉም።

እሱም ማጣራት ያስፈልገዋል ማለታቸው ተገልጿል።