(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 26/2011)የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ተቃዋሚው ዶክተር ሪክ ማቻር በአዲስ አበባ በሰላም ጉዳይ ላይ ሊወያዩ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አደራዳሪነት የሚካሄደው የሰላም ውይይት በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ችግር እንደገና ይገመግማል ተብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 3/2019 በአዲስ አበባ ይካሄዳል በተባለው የሰላም ውይይት በቅድመ የሽግግር ጊዜ ይፈጸማል የተባለው ስምምነት ተግባራዊ አለመሆኑን ይመለከታል ተብሏል።
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንትና የአማጺው መሪ ዶክተር ሪክ ማቸር የሰላም ውይይቱ ጥሪ በኢጋድ አማካኝነት እንደደረሳቸው ለማወቅ ተችሏል።
በ8 ወራት ተግባራዊ እንዲሆን በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ተደርጎበት የቆየው የቅድመ ሽግግር ጊዜ በታቀደለት ሁኔታ ሳይሳካ ከ2 ሳምንታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከተቀዳጀችና እንደ ሃገር ከተመሰረተች በኋላ የሰላም ስምምነት ተደርጎ ሪክ ማቸር ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ እንደገና በተፈጠረ አለመግባባት ሃላፊነታቸውን ለቀው እንደገና ወደ አማጺነት መመለሳቸው ይታወሳል።