የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገበት ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2011)የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገበት መሆኑ ተገለጸ።

ለ17ዓመታት ሲሰራበት የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መከለስ ያስፈለገው የዓለም ሁኔታዎች በመቀየራቸው ነው ተብሏል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ክለሳው የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የተዘጋጀና ዝርዝር ጉዳዮች የተካተቱበት ይሆናል።

ኤርትራን በተመለከተ ፖሊሲው ይዞት የነበረው አቋምም ይከለሳል ሲሉ ገልጸዋል።

ከኤርትራ ጋር የሚያዋስኑ ድንበሮች መዘጋታቸውን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሁለገብ ግንኙነት ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው በመስራት ላይ ነው ከማለት ያለፈ ምላሽ አልሰጡም ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በውጭ ጉዳይና በሃገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ሲጠበቅ ነበር።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክፍተቶች ያሉበት ግልጽ የሆነ አካሄድ የማይታይበት ነው የሚል የባለሙያዎች ጠንካራ ትችትን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህን ክፍተት በሚገባ የተገነዘበው እንደሆነ ነው መረጃዎች ያመለከቱት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት በሥራ ላይ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ የቆየና አላስፈላጊ ዝርዝሮችን የያዘ ነው።

በይዘት ደረጃ በደረግ ዘመን የነበረው የተሻለ እንደሆነ ነው ዶክተር ማርቆስ የሚገልጹት በመሆኑም የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ፖሊሲውን መከለስ ያስፈገው የዓለም ሁኔታዎች በመቀየራቸው ነው።

አቶ ነቢያት እንደሚሉት ደቡብ ሱዳን የተሰኘች አዲስ ሀገር ተፈጥራለች።

በኤርትራ አንጻርም ስሟ ተጠቅሶ በፖሊሲው የተቀመጠው መስመር አሁን ካለው ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይደለም።

ሌሎች ዓለም አቀፍ የሆኑና ድንበር ዘለል ጉዳዮችን በማካተት በአዲሱ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዘመኑን የሚመጥን አካሄድ ለመከተል በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት

አዲስ የሚዘጋጀው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን የሚያካትት እንደሚሆን አቶ ነቢያት ገልጸዋል።

ይህም በውጭ ሀገራት በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን ነው ቃል አቀባዩ ለኢሳት የተናገሩት።

80 በመቶ የክለሳው ስራ መጠናቀቁን የገለጹት ቃል አቀባዩ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚቀየር ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኤርትራ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች በኤርትራ መንግስት በኩል ድንበሮቹን በመዝጋት የተወሰደውን ርምጃ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው እያዘጋጀን ያለነው ተቋማዊ አሰራር አልተጠናቀቀም።

ወደፊት አሰራሩ ወደተግባር ሲለወጡ ችግሮቹ የሚፈቱ ይሆናሉ። ከዚያ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም ይላሉ።