(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2011)በአሜሪካ ሁለት ኢትዮጵያውያንን በመግደል ወደኢትዮጵያ አምልጧል በሚል በተጠርጣሪነት የሚፈለግን ግለሰብ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሳልፎ እንዲሰጥ መወሰኑ ውዝግብ አስነሳ።
ዮሀንስ ነሲቡ የተባለና የአሜሪካ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የ25 ዓመት ወጣት በአሜሪካን ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ ሁለት ወጣቶችን በመግደሉ አሜሪካ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረ መሆኑ ተመልክቷል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ሳይኖራቸው ተጠርጣሪውን ለአሜሪካ ለመስጠት በአቃቤ ህግ የተላለፈው ውሳኔ ህገወጥ ነው ሲሉ የተጠርጣሪው ጠበቆች ተቃውመዋል።
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ታህሳስ 2008 ነው። በአሜሪካን ቨርጂኒያ ግዛት አንድ ኢትዮጵያዊ በጥይት ተመቶ ይገደላል።
የሴት ጓደኛውም በቅርብ ርቀት በሚገኝ ስፍራ በጥይት ጭንቅላቷን ተመታ አንገቷ በገመድ ታንቆ ከዛፍ ጋር ታስራ ትገኛለች።
ድርጊቱ በግዛቷ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ ነበር።
ግድያውን ፈጽሟል ተብሎ የሚጠረጠረው ደግሞ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ወጣት ነው።
ዮሀንስ ነሲቡ የተባለው ወጣት ሁለቱን ኢትዮጵያውያን ከገደለ በኋላ በአሜሪካን አልቆየም። ወዲያውኑ ወደትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተሳፍሮ ይሄዳል።
የቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ አውራጃ ፖሊስ ጉዳዩን በነፍስ ግድያና በገንዘብ ዘረፋ ወንጀል ፋይል በመክፈት ክትትል ይጀምራል።
ተጠርጣሪው ዮሀንስ ነሲቡ ግን ወደኢትዮጵያ በማምራቱ ለአሜሪካን መርማሪዎች ሂደቱን ለመቀጠል የሚችሉት አልሆነም።
ወደኢትዮጵያ ማምራቱን አሜሪካኖቹ መርማሪዎች ካረጋገጡ በኋላ ጉዳዩ ተዳፍኖ መቅረቱን ነው የሟቾች ቤተሰቦች የሚገልጹት።
ተጠርጣሪው ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ በነጻነት እንደሚንቀሳቀስ መረጃው እንዳላቸው የሚገልጹት የሟች ቤተሰቦች የፍትህ ያለ ጥያቄ ለሁለቱ ሀገራት መንግስታት በማቅረብ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ይሁንና በሁለቱ ሀገራት መካከል ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባለመኖሩ ጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረቱን ቤተሰቦች ይገልጻሉ።
ተጠርጣሪው ዮሀንስ በቲውተር ገጹ አደገኛ የሆኑና ሴትን ልጅ መግደልን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን ያስተላልፍ እንደነበረ የአሜሪካን መርማሪዎች መግለጻቸውን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።
ባለፈው የካቲት ወር ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ አማካኝነት ጉዳዩ ዳግም መነሳቱን የሚገልጹት ቤተሰቦች በመጨረሻም ተጠርጣሪው ዮሀንስ ነሲቡ በቁጥጥር ስር ተደርጎ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት መታየት መጀመሩ ታውቋል።
የአሜሪካን ኤምባሲ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተጠርጣሪው ለአሜሪካን ተላልፎ እንዲሰጥ ውሳኔ ተላልፏል።
ውሳኔው ግን ውዝግብ ማስነሳቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
የኢትዮጵያ መርማሪዎች ወንጀሉ ባልተፈጸመበት ሀገር አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ የማይችሉ በመሆናቸው ተጠርጣሪው ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤት ተገልጿል።
ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረው ፍርድ ቤትም በፖሊስ የተጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱ ታውቋል።
የተጠርጣሪው ጠበቆች የኢትዮጵያ ፖሊስ በሌላ ሀገር የተፈጸመን ወንጀል የመመርመር መብት የላቸውም ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን በአቃቤ ህግ የተወሰነው ተላልፎ የመሰጠት ውሳኔ ህገወጥ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲያግደው ጠይቀዋል።
የተጠርጣሪው ጠበቆች በኢትዮጵያና በአሜሪካን መሀል ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በሌለበት ሁኔታ የአቃቤህግ ውሳኔ ህጋዊነት የለውም ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ተላልፎ የመስጠት ውሳኔ በፖሊስ ስላልቀረበልኝ በሚል የተጠርጣሪው የአካል ደህንነት መብት እንዲጠበቅ በማዘዝ መዝገቡን መዝጋቱ ታውቋል።
ቀጣዩ ርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠቅላይ አቃቤ ህግ ምላሽ እየጠተበቀ ነው ተብሏል።