ጎሰኝነት በህግ ይታገድ በሚል የማህበራዊ ድረ ገጽ ዘመቻ ተከፈተ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2011)ጎሰኝነት በህግ ይታገድ በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ መከፈቱ ታወቀ።

በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የዘር ፖለቲካ እንዲታገድ የሚጠይቅ ትዕይንተ ህዝብ ሊያደርግ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል።

ከትላንት ጀምሮ በፌስ ቡክ፣ በቲውተርና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች በተጀመረው ዘመቻ ኢትዮጵያን ለአደጋ ያጋለጠ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዜጎቿን ለመፈናቀልና ለግድያ የዳረገው የጎሳ ፖለቲካ በህግ እንዲታገድ የሚጠይቁ መልዕክቶች በመተላለፍ ላይ ናቸው።

በመንግስት የተጀመረው የማሻሻያ ስራ የጎሳ ፖለቲካን ካላገደ ትርጉም የለውም ሲሉ አዘጋጆቹ ባሰራጯቸው መልዕክቶች ገልጸዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የተጠራው ሰልፍም በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ጎሳን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ ስርዓት ኢትዮጵያን ለአደጋ አጋልጧል ነው የሚሉት የዘመቻው አስተባባሪዎች።

ስርዓቱ ባለፉት 27 ዓመታት በመንግስት መዋቅር ህጋዊነትን ተላብሶ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ሲያጋጭ ነው ለበርካቶች መሞት ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪዎች እንደሀገር ኢትዮጵያ እንዳትቆም ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን ይጠቅሳሉ።

ለጎሳ ፖለቲካ እውቅና በመስጠት የዜግነትን መብት የገፈፈው ህገመንግስቱ በአፋጣኝ እንዲከለስ የሚጠይቀው ዘመቻው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከዚህ አንጻር ጊዜ የማይሰጠው ሃላፊነት ከፊቱ ይገኛል ሲል ያሳስባል።

መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ቃል ቢገባም የጎሳ ፖለቲካን የማያግድ ማሻሻያ ትርጉም አይኖረውም ሲሉ ዘመቻውን የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክና በቲዎተር ገጾቻቸው መልዕክቶችን እያሰራጩ ነው።

ዘመቻውን በማስተባበር ላይ ያሉትም የዘመቻው ዓላማ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጭምር አላሰራና አላንቀሳቀስ ያለውን የጎሳ ፖለቲካ ለማገድ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ለማድረግ ነው ብለዋል።

ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ከባዱ በላቸው ሀገሪቱ ላይ እውነተኛና ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መንግስት ቁርጠኛ ከሆነ ቀጣዩ እርምጃው የጎሳ ፖለቲካን በህግ ማገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው ዘመቻ ተሳታፊዎች የተለያዩ በፎቶግራፎችና በጽሁፎች የታጀቡ መልዕክቶችን በማጋራትና በማሰራጨት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በተመሳሳይ በፈረንጆቹ ግንቦት 6 ከአንድ ሳምንት በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል ትዕይነተ ህዝብ መጠራቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተጠራው ሰልፍ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲታገድ የሚጠይቅ ነው።

ለዚህ የጎሳ ፖለቲካ እውቅና የሰጠው ህገመንግስቱም እንዲቀየር በሰላማዊ ሰልፉ እንደሚጠይቅ ታውቋል።