የጌዲዮ ተፈናቃዮች ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ ወደ ቀያቸው እንደማይመለሱ መናገራቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2011)የጌዲዮ ተፈናቃዮች ወደ ቀያችሁ ተመለሱ የተባልንው ምንም ቅድመ ሁኔታ ባልተሟላበት ሁኔታ ውስጥ ነው ሲሉ ለኢሳት ገለጹ።

እስካሁንም አንድም ተፈናቃይ ወደ ቀየው አለመመለሱንም ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል።

እርቅና ሰላም ተፈጥሯል በሚል እየተናፈሰ ያለውም ወሬ ከእውነት የራቀና ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እየተራገበ ያለ ወሬ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ትላንት ከቀያችን ያፈናቀሉን፣የገደሉንና ያረዱን ሰዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ ዛሬም እነሱ የእኛ አስመላሽ ሆነው ሲሯሯጡ ማየት ወደቀያችን የመመለሱን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ።

የጌዲዮ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ መጀመሩንና በ15 ቀናት ውስጥም ወደ 500ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢው ለመመለስ እቅድ መያዙን መግለጹ ይታወሳል።

ይህንን ስራ ተግባራዊ ለማድረግም ለተፈናቃዮቹ ጋር መነገሩንና ጉዳዩንም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እርቅ መደረጉን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ሰፍረዋል።

ተፈናቃዮቹ የተፈጠረው አንድ መድረክ ነበር በዚህም መድረክ ላይ ያነሳንው ጥያቄ ካልተመለሰ ወደ ቀያችን የመሄዱ ጉዳይ አደጋ እንዳለው መናገራቸውን ይገልጻሉ።

ለመፈናቀሉ ምክንያት የሆኑና የሰውን ህይወት ያጠፉ ግለሰቦች እስካሁን ለፈርድ አልቀረቡም ይላሉ ተፈናቃዮቹ።ዛሬ ላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው አስመላሽ ሆነው መምጣታቸውን በመጠቆም።

በእርቅ ጉዳዩ ተፈቷል በሚል በመገናኛ ብዙሃን የሚራገበው ወሬም ቢሆን ከእውነት የራቁና የሚለቀቁትም ቪዲዮዎችም ቢሆኑ ከዚህ በፊት ተካሄደው ህዝብን ለመታረድና ለመገደል ያበቁ ናቸው ሲሉም በምሬት ይናገራሉ።

ተፈናቃዮች እንደሚሉት እስካሁን አንድም ተፈናቃይ ወደ ቀዬው አልተመለሰም።

ተፈናቃዩ ያቀረባቸው መሰረታቂ ጥያቄዎች ቢኖሩም እስካሁን ለአንዱም ምላሽ አልተሰጠም ይላሉ።

የእርዳታውም ጉዳይ ቢሆን እንደሚባለው አይደለም እስካሁንም ያለንው የከፋ ሁኔታ ውስጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል።