(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2011) የአማራ ክልላዊ መንግስት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን አዲስ አበባን በተመለከተ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት ዙሪያ ማብራሪያ የሚሰጥ መግለጫ አወጣ።
ክልላዊ መንግስቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በህግ አግባብ ለመምራት በሚደረገው ጥረት ከኦሮሚያ ክልል ጎን ተሰልፎ የመታገል ጉዳይ ከመርህ ውጭ እየተተረጎመ ነው ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
በቅርቡ በአምቦ ከተማ ተካሄዶ በነበረው የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ላይ ርእሰ መስተዳደሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅሟ እንዲከበር በሕገ መንግስቱ መሰረት እንታገላልን ማለታቸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ትችትን ማስከተሉ ይታወሳል።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር እና ግንኙነትን ማጠናከር ከችግሮች ማርከሻ መካከል አንደኛው መድሃኒት ተደርጎ ይወሰዳል ሲል የአማራ ክልል መንግስት መግለጫ አመልክቷል።
ግንኙነቱን አስመልክቶ አሁን ላይ አዎንታዊም አሉታዊም በሆነ መልኩ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ውስጥ የተለያዩ ስሜቶች መስተዋላቸውን አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥቷል።
ለመግለጫው መውጣት ምክንያት የሆነው ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶር አምባቸው መኮንን አዲስ አበባን በተመለከተ በቅርቡ የሰጡት አስተያየት ነው።
በአምቦ በተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ዶክተር አምባቸው መኮንን የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ ከተሳታፊ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
በዚሁም አዲስ አበባን በተመለከተ ባለቤቶቹ ነዋሪዎቿና ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው የሚል ምላሽ ቢሰጡም ልዩ ጥቅምን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ግን ውዝግብ አስከትሎባቸዋል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያላትን ልዩ ጥቅም በህገመንግስቱ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን እንታገላለን ማለታቸው ነው።
እናም ይህንኑ አስመክቶ የአማራ ክልላዊ መንግስት በሰጠው መግለጫ እንዳብራራው ህገ-መንግስቱን መፈተሽ፤ ማሻሻል እና ማስተካከል ይገባል ብሏል።
ይህም ሆኖ ግን መሻሻል የሚገባቸው ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ሕዝቡን ባሳተፈ እና በዴሞክራሲያዊ አግባብ እስኪሻሻሉ ድረስ የምንመራበት ሰነድ መሆኑን ጭምር እናምናለን በማለት በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን በአዲስ አበባ ላይ ኦሮሚያ ያላትን ጥቅም በተመለከተ በህግ መቀመጡ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል ብሏል፡፡
ይሕን ሀሳብ ዶክተር አምባቸው በማረመዳቸውም የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ በማለያየት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት ግንኙነቱን በማጠልሸት ላይ መጠመዳቸው የኖረ፤ ያለና የሚኖር ሀቅ ነው ብሏል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በከፊል የሚቀበል መስሎ ነገር ግን በይዘት ደረጃ የተወሰኑ ጉዳዮችን በመምዘዝ ከትልቁ ስዕል እየወጡ ሆን ብለውም ሆነ ሳይረዱት ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ዱላ ማቀበል ላይ የሚታትሩ መኖራቸውንም ተገንዝበናል ብሏል መግለጫው፡፡
በህገ-መንግስቱ መሰረት ልዩ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ የተቀመጠ ባለመሆኑ ሁላችንም የራሳችንን ፍላጎት በላዩ ላይ ጭነንበት በየአቅጣጫው የምንጓተተው ጉዳይ ሆኗል ሲልም ነው ያመለከተው ፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖረው የኦሮሞ አርሶ አደር ከተማው ሲያድግና ሲሰፋ የአርሶ አደሩን መብት በመዋጥ ላይ የሚመሰረት ከሆነ ትክክል ስለማይሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ የአርሶ አደሮች መብት እንዲከበር በሚደረገው ትግል ጥያቄውን ደግፎ ለመታገል የግድ ኦሮሞ መሆንን አይጠይቅም ሲልም ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ጉዳይን አስመልክቶ፤ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በህግ አግባብ ለመምራት በሚደረገው ጥረት ከኦሮሚያ ክልል ጎን ተሰልፎ የመታገልን አስፈላጊነትም ገልጿል።
በመሆኑም ትልቁ ስዕል መሆን ያለበት በሁለቱ ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም ብሏል፡፡
በዚህ ሂደት የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች እና የሕዝብ አንቂዎች (Activists) ጋር ተናቦ እና በመተጋገዝ መስራት የአማራን ሕዝብ ፖለቲካ ወደፊት እንዲራመድ ያደርገዋል ነው ያለው፡፡
በመሆኑም ለአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ይህን ወቅት በአሸናፊነት ለመሻገር እርስ በእርሳችን ተጠላልፈን ከመውደቅ አጉል በሽታ ወጥተን በጋራ ክንዳችን ለሕዝባችን አጀንዳዎች መሬት መንካት በትላልቅ ስዕሎች ላይ ተመስርተን ዴሞክራሲያዊ ትግል፤ ትብብር እና አብሮነትን እንድናዳብር ለመላው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን ሲል የአማራ ክልል መግለጫ አመልክቷል።