ዶክተር ሰገነት ቀለሙ በካንሳስ ዩንቨርስቲ እውቅና ተሰጣቸው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2011)በእርሻ ምርምር ስራ የሚታወቁት ዶክተር ሰገነት ቀለሙ በሙያቸው ካላቸው የላቀ እውቀትና ባደረጉት አስተዋጽኦ በካንሳስ ዩንቨርስቲ እውቅና ተሰጣቸው።

ዶክተር ሰገነት ያገኙት ዓለም አቀፍ እውቅና ከ12 ሰዎች መካከል ከተመረጡትና ከ5 ሴቶች መካከል አንዷ ሆነው በመመረጣቸው መሆኑን ዩንቨርስቲው አስታውቋል።

የካንሳስ ግዛት ዩኒቨርሲቲ የአልሙኒ መርሃግብር ምክትል ፕሬዝዳንት አንድሪያ ብሪያንት ዶክተር ሰገነት በስራቸውና በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ የላቀ ተግባርና ውጤታማ የምርምር ስራ በማከናወናቸው የተመረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰብል ተባይ ላይ ምርመር የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ማዕከል ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ሰገነት የዶክትሬት ትምህርታቸውን በተከታተሉበት የካንሳስ ግዛት ዩኒቨርስቲ የተሰጣቸውን እውቅና አስመልክቶ እንደተናገሩት ይሄ ለእኔ ታላቅ ክብር ነው።

በኢትዮጵያ የገጠር ክፍል ስላደኩኝ ህብረተሰቡ የሚገጥመውን የዕለት ተዕለት ችግር በሚገባ እረዳዋለሁ።

ከሰብል ተባይ ጋር የሚደረገውን ግብግብ አውቃዋለሁ። የእኔ ራዕይ በሙያዬ ይህን ለመርዳት የምችልበትን ውጤታማ ምርምር ማድረግ ነው።

ይህ እውቅና ትልቅ ጉልበት ይሰጠኛል ብለዋል። ዶክተር ሰገነት የካንሳስ ዩኒቨርስቲን ክብር በማግኘት ብቸኛዋ አፍሪካዊ ተመራማሪ መሆናቸውም ታውቋል።