(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2011)በኢትዮጵያ አሁን ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ጽንፍ የያዘ ብሄርተኝነት አንደኛው ነው ሲሉ የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ገለጹ።
እናም በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መካከል ሊደረግ የታሰበው ውህደት ይሕን ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
ወሕደቱ ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ጋር ፣ ከፌዴራል ስርዓቱና በህገ መንግስቱ ከተቀመጡ የመንግስት አስተዳደር ጉዳዮች ጋር እንደማይጣረስም ኣአቶ መለሰ አለሙ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ውህደቱ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ለህዝቦች ትስስር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
አቶ መለስ እንዳሉት የድርጅቱን ድክመት በማስወገድ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማጎልበትና የሀገሪቱን ህዳሴ ማፋጠን ኢህአዴግ ስለውህደቱ እንዲያስብ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ፡፡
እንደ አቶ መለስ ገለጻ አሁን ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ጽንፍ የያዘ ብሄርተኝነት አንዱ ነው ።
ኢህአዴግ የብሄር ማንነት ላይ በሰራው ስራ ዜጎች ማንነታቸው እንዲከበርና በማንነታቸው እንዲኮሩ ከማድረግ አንጻር የተሳካ ስራ ቢሰራም ብሄራዊ ማንነትና ሀገራዊ ማንነት ማስተሳሰር ላይ ግን ክፍተት ነበር ብለዋል፡፡
ይህን በመረዳትም በተጀመረው ለውጥ ለኢትዮጵያ ማንነት ትኩረት ተገርጓል ነው ያሉት።
አሁን የሚመሰረተው ውህድ ፓርቲም ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካተቱበት በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
አቶ መለስ እንደገለጹት ውህደቱ የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እውን ለማድረግና ማህበራዊ ትስስሩን ለማጠናከር ብሎም አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ያስችላል ፡፡
በድርጅቱ ውስጥ ይህ ሃሳብ መነሳት ከጀመረ አስር አመት ገደማ ሆኖታል ያሉት ምክትል ሃላፊው ባሳላፍነው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔም መፋጠን እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ጉባዔዎች ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረ ሃሳብ እንደሆነ በመጠቆም የጉባዔ ውሳኔ ማለት የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውሳኔ ስለሆነ ድርጅቶቹ በዚህ ላይ ምንም ልዩነት አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
ውህደቱ የሚካሄደው በኢህአዴግ አባልና አጋሮቹ መካከል መሆኑም ገልጸዋል።
አቶ መለስ ለኤፍቢሲ ዘጋቢ እንደገለጹት ኢህአዴግ እንደተራማጅ ፓርቲ በሃሳብ ከሚቀራረቡት ጋር አብሮ ለመስራትም ሁሌም በሩ ክፍት ነው፡፡