ኢትዮጵያ አንድ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጥ ሳተላይት ልታመጥቅ ነው

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2011)ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጥ ሳተላይት እንደምታመጥቅ ተገለጸ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ ሳተላይት ከሌላ ሀገር  ወደ ህዋ ለማምጠቅ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።

የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት ወደ ህዋ የማምጠቅ ሙከራ ለማድረግ የሳተላይት ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ ፣ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ለአገሪቱ የመጀመሪያው የሚሆነውን የመረጃ ሳተላይት ከሌላ ሀገር ለማምጠቅ የዝግጅት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሳተላይት የምታመጥቀው በአገር ውስጥ አለመሆኑ ቢገለጸም ሳተላይቱን ዲዛይን የማድረግና የመገንባት ሥራ ከሞላ ጎደል በኢትዮጵያውያን የተከናወነ ነው ተብሏል።

በርካታ የውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች የዕውቀት ሽግግሩን በከፍተኛ ደረጃ መደገፋቸውን፣ በአሁኑ ወቅትም ከሃምሳ በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን በህዋ ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የመጀመሪያውን ሳተላይት ለማምጠቅ ከስምንት ሚሊዮን ዶላር ባላይ ወጪ መደረጉንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በመጪው ዓመት እስከ ህ   ዳር ወር ድረስ ይመጥቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የመረጃ ሳተላይት፣ በዋናነት ለመሬት ምልከታ ሥራ ላይ እንደሚውል ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የሳተላይት ማምጠቅ ሥራው በስኬት ከተጠናቀቀ መንግሥት ለግብርና፣ ለውኃ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለማዕድን ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል የሚሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ ከሳተላይቱ ማግኘት እንደሚያስችለውም ነው የገለጹት።

በራስ አቅም የተጀመረውን የህዋ ምርምርና ተጨማሪ ሳተላይት የመገንባት አቅም የበለጠ ለማጎልበት፣ የሳተላይት ግንባታ ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ለሳተላይት ፋብሪካ ግንባታ ከሚደረገው ዝግጅት በተጨማሪ፣ የመገጣጠሚያና የፍተሻ ማዕከል ለመገንባትም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተጨማሪ የሳተላይት መረጃ መቀበያ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ በማስፈለጉም፣ የግራውንድ ስቴሽን ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ዶር ጌታሁን ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ማዕከል ግንባታና የመሣሪያዎች ተከላ ተጠናቆ በመጪው ዓመት መጀመርያ ሥራ እንደሚጀምር፣ ይህም ከሳተላይ በሚደረግ የመሬት ምልከታ የሚሰበሰብ የመረጃ ፍላጎትን 50 በመቶ ይመልሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጻቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡