በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ላይ የሚካሄደው ማስፈራራትና ዛቻ በአስቸኳይ እንዲቆም ተጠየቀ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2011)በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ላይ የሚካሄደው ማስፈራራትና ዛቻ በአስቸኳይ እንዲቆም ከ40 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን እና  ታዋቂ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ደብዳቤ ጻፉ።

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና ዶክተር አክሎግ ቢራራን ጨምሮ ከ40 በላይ ምሁራን ለዶክተር አብይ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ታጋዩ እስክንድር ነጋ የራሱን የግል ሕይወት ትቶ ለሃገሩ ዋጋ የከፈለና አሁንም በሰላሚዊ መንገድ የሚታገል ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነው ብለዋል።

እናም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ሆኖ ያደረገው ሰላማዊና ጨዋነት የተሞላበት ውይይትና አቤቱታ ያስመሰግነዋል እንጅ አድናቂዎቹንና ደጋፊዎቹን የሚያስወቅስ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ምሁራኑ ድጋፋቸውን ገልጸውለታል።

ምሁራኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አስመልክተው በጻፉት ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለዲሞክራሲ ስርአት መጎልበት የጀመሩት የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ ግን በዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ብቻ የተፈናቀሉት ከሶስት ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ተመልሰው እንዲቋቋሙ ሳይደረግ ሌሎች በብዙ ሺህ የሚገመቱ ወገኖቻችን ለተመሳሳይ አደጋ መጋለጣቸው እጅግ በጣም አሳስቦናል ነው ያሉት።

እናም ይህ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያናክስና አገርን የሚያፈርስ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲቆም ያልተቆጠበ ጥረት ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል። —ምሁራኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ።

የዚህ ደብዳቤያቸው ዋነኛ ትኩረት ግን በአዲስአበባ ላይ የተከሰተውን ችግር መነሻ በማድረግ  በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰነዘሩት ማስፈራሪያና ዛቻ ነው።

እንደ ምሁራኑ ገላጻ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሚመለከታቸው ነዋሪዎች ጋር ሆኖ ያደረገው ሰላማዊና ጨዋነት የተሞላበት ውይይትና አቤቱታ ያስመሰግናል እንጅ አያስወቅስም።

ሆኖም ግን እስክንድር ነጋን እና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ወዳጆቹን እንዲሁም  አድናቂዎቹንና ደጋፊዎቹን ማስፈራራትና መዛት ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የቆመለት ጉዳይ የግል ዝና ወይንም ጥቅም ሳይሆን የሁላችንም ጉዳይ መሆኑን ልናስምርበት እንፈልጋለን ሲሉም ምሁራኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል ።

እንደ ምሁራኑ ገላጻ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተከሰተው አለመግባባት ለሁሉም አስደንጋጭ የሆነና የባለቤትነት ጥያቄውም የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጅ የእስክንድርና የደጋፊዎቹ ብቻ አይደለም።

የአዲስ አበባ ጉዳይ የአንድ ዘውግ ወይንም የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎ የመላው የጥቁር አፍሪካ ሃገራት ጉዳይም ነው ብለዋል።

እናም በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ዳጋፊዎቹ ላይ የሚካሄደው ዛቻና ማስፈራራያ እርስዎና መንግሥትዎ ከቆማችሁለት መንፈስ ጋር ይጋጫል ሲሉ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ምሁራኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ እስክንድር ነጋ ዓለም ያደነቀውና ያከበረው ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ ክብርና ሽልማት ያገኘውም ቤተሰቡን ወደ ጎን ትቶ፤ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ ዘውግና ኃይማኖት ሳይለይ እስካሁን ለቆመለት የተቀደሰ ዓላማ የሚታገል በመሆኑ ነው ብለዋል።

እናም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለፉት ሃያ ስድስት አመታት የከፈለውን ዋጋና ያበረከተው አስተዋጽኦ ሊረሳ አይገባም ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ሕዝብ መመራትና መተዳደር ያለበት ነዋሪው ሕዝብ በመረጣቸው ሃላፊዎች መሆን አለበት ያሉት ምሁራኑ ጋዜጠኛ እስክንድር የጠየቀውም ከዚህ የተለየ አይደለም ብለዋል።

ስለሆነም በእስክንድር ነጋ ላይ የሚካሄደው ማስፈራራትና አላስፈላጊ ዛቻ በአስቸኳይ እንዲቆምና በሕይወቱ ላይም አደጋ እንዳይደርስበት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደብዳቤ የጻፉት ከ40 በላይ ምሁራን ጥሪ አቅርበዋል።