(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2011)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም 331 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከተፈቀደለት በጀት ውጭ መጠቀሙን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አጋለጠ ።
ሚኒስቴሩ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከመጠቀሙ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴርን ፈቃድ ማግኘት እንደነበረበትም ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2009 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝትን ገምግሟል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2009 ዓም 331 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከተፈቀደለት በጀት ርዕስ ውጭ የገንዘብ ሚኒስቴርን ፍቃድ ሳያገኝ በጀት አዛውሮ መጠቀሙ በኦዲት ተረጋግጧል።
ሚኒስቴሩ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከመጠቀሙ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴርን ፈቃድ ማግኘት ነበረበት ያሉት ዋና ኦዲተሩ “ይህን ባለማድረጉ መንግሥት ያጸደቀውን የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ተጥሷል ፤ ይህም በህግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው” ሲሉ ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንዲያውለው ከተመደበለት አጠቃላይ በጀት ውስጥ 445 ሚሊዮን ብር አለመጠቀሙንም የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ለሰንዓ ፎረም ተብሎ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ጸድቆ እንዲወጣ ተደርጓል።
ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ የሚገልጽ ማስረጃ ሳይቀርብ ክፍያ መፈጸሙን በኦዲት ምርመራ እንደተደረሰበትም አቶ ገመቹ አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ በካንቤራ፣ በብራስልስና በዋሽንግተን ውል ሳይታሰር እንዲሁም ከመንግስት የግዢ አዋጅ ውጭ ያለ ውድድር ከአንድ አቅራቢ የአምስት ሚሊዮን 953 ሺህ ብር የተለያዩ ግዢዎች መፈጸማቸውን ምርመራው አረጋግጧል።
የፌደራል መንግስት የግዢ ስርዓትን በጣሰ መልኩ አንድ ሚሊዮን 894 ሺህ ብር የተለያዩ የአገልግሎት ግዢዎች መፈጸማቸውንም አብራርተዋል።
በ2009 በጀት ዓመት በአሜሪካና በካናዳ በሚገኙ ግዛቶች የተደረገን ጉዞ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የተደረገ ጉዞ በሚል ከመንግስት መመሪያ ውጪ ለመልካም አገልግሎት ክፍያ ለዲፕሎማቶች የተከፈለው ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ መደረግ እንዳለበት ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ሚኒስቴሩ ማስረጃ ሳያቀርብ ለሚፈፅማቸው ክፍያዎች በቂ ማስረጃ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ እያቀረበ አይደለም ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በኦዲት ግኝቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም የሚቆይ የድርጊት መርሃ ግብር ቀርጾ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ አብዛኞቹን ስራዎች የሚያከናውነው በውጭ አገሮች በመሆኑ ስራ የሚስራባቸው አገሮች የፋይናንስ ህጎች ከአገሪቱ ጋር አለመጣጣም እንቅፋት እየሆነበት መሆኑን አስረድተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ በሰጡት ማጠቃለያ በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የቀረቡ ክፍተቶችን በማጤን አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።