የአባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ በደጀን ወረዳ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2011) በአማራ ክልል በዓባይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ሊሰሩ ከታቀዱ 20 ኢንዱስትሪዎች አንደኛው የሆነው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ በደጀን ወረዳ ተጀመረ።

የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በአማራ ክልል ኢንዳስትሪዎችን ለማስፋፋት ከግል ባለሀብቱ ጋር የክልሉ መንግሥት የጋራ ጥምረት ፈጥሮ  እየሰራ ነው ብለዋል።

በደጀን የተጀመረው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ክ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግበት ተገልጿል።

በደጀን ወረዳ ሰሳ በራይ ቀበሌ የሚገነባው ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እኝደሚያመርት ይጠበቃል። ግንባታው ሲጠናቀቅም ከ1500 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው።

ለአጠቃላይ ግንባታውም 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጭ እንደሚደረግም ታውቋል።የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በአማራ ክልል ኢንዳስትሪዎችን ለማስፋፋት ከግል ባለሀብቱ ጋር የክልሉ መንግሥት የጋራ ጥምረት ፈጥሮ  እየሰራ ነው ብለዋል።

‹‹ትግል እና ልማት እንደዱላ ቅብብሎሽ ነው›› ያሉት ዶር አምባቸው መኮንን የተበታተነውን አቅም እና ገንዘብ አቀናጅቶ በመያዝ የታቀዱ ከ20 በላይ ኢንዳስትሪዎች ከዓባይ ኢንደስትሪ አክስዮን ማኅበር ጋር እንደሚሠሩም ነው የገለጹት።

መሬት፣ ብድር እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ኢንዳስትሪውን ለማስፋፋት ቁልፍ ጉዳዮች በመሆናቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድን ማስፋፋት እና መደገፍም ትኩረት እንደሚደረግበትም ነው ያስታወቁት፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ቢሮ ኃላፊ እና የዓባይ አክስዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል ‹‹ለፋብሪካው 311 አርሶ አደሮች መሬታቸውን 38 አርሶ አደሮች ደግሞ ቤታቸው የነበረበትን ቀያቸውን ለልማቱ ሲባል በፈቃደኝነት ለቀዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ለእነዚህ ተነሺ አርሶ አደሮች ሌላ ቦታ ላይ በማስፈር ውኃ፣ መንገድ፣ የመብራት ኃይል እና መሠረተ ልማት አሟልቷል ሲሉም ገልጸዋል።

ለተነሽ አርሶ አደሮቹ 123 ሄክታር ተለዋጭ መሬት እና 71 ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉንም ነው የገለጹት፡፡

አቶ መላኩ ፕሮጀክቱ በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።

የክትትል ሥራውን የዴንማርኩ ኤፍ. ኤል. ስሚዝ ኩባንያ እና የሲቪል ሥራውን የቻይናው ሄንግዮአን ኩባንያ እንዲሠሩት የውል ስምምነት መፈፀሙን መግለጻቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።