በሳውላ ማረሚያ ቤት የታሰሩ ወጣቶች ያለፍትህ እየተሰቃዩ መሆናቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2011)በጎፋ ዞን ሳውላ ማረሚያ ቤት የታሰሩ ወጣቶች ያለምንም ክስ ከአራት ወራት በላይ በእስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ መሆናቸው ተገለጸ።

ኢሳት እንደደረሰው መረጃ ከሆነ ቁጥራቸው 50 የሚደርሱት ወጣቶች የታሰሩት ባለፈው ህዳር 2011 ነው።

በነዚህ ጊዜያት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉት ወጣቶች በእስር ቤት ውስጥ የሚፈጸምባቸው ድብደባና ኢሰብአዊ ድርጊት ለከባድ የጤና ችግር እያጋለጣቸው መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የጎፋ ዞን ነዋሪዎችም ድጋፋቸውን ሊገልጹ አደባባይ ይወጣሉ።

በዛ የድጋፍ ሰልፍ ላይም የቀድሞ አመራሮችን ምንም አልሰራችሁልንም በሚል ተቃውሞውን ፎቷቸውን በማቃጠል ይገልጻል ይላሉ ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩትና ለኢሳት መረጃውን ያደረሱት የአካባቢው ነዋሪ።

ያ የተቃውሞ ጉዳይ ለወጣቶቹ መታሰር ምክንያት እንደሆነና ፎቷቸው የተቃጠለባቸው ባለስልጣናት ወጣቶቹ እንዲታሰሩ እጃቸው እንዳለበት ማስረጃ አለን ይላሉ ።

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ወጣቶቹ ባለፈው ህዳር 2011 በጎፋ ዞን ሳውላ ማረሚያ ቤት ሲታሰሩ ቁጥራቸው ወደ አንድ መቶ ይደርስ ነበር።

የተወሰኑት በዋስ ሲፈቱ ሌሎቹ ወደ 50 የሚደርሱት ግን አሁንም በእስር ቤት ስቃያቸውን እያዩ ነው ብለዋል።

በእስር ቤት ከሚደርስባቸው ድብደባ ጋር ተያይዞም ለከፋ የጤና ችግር መዳረጋቸውን ነው የገለጹት።

ታሳሪ ወጣቶቹ የታሰረንበት ጉዳይ ይገለጽልን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው ወገን እንዳላገኙም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ከአራት ወር የእስር ቆይታ በኋላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቢደረግም ከችሎቱ ግን ያገኙት ምንም ምላሽ የለም ብለውናል።

በቀጠሮ እንዲሰናበቱ የተደረጉት ወጣቶች መብታችን ይከበር አላግባብ የሚደርስብን ስቃይ ይቁም በሚል ድምጻቸውን ቢያሰሙም ፖሊስ ለማስፈራሪያ በከፈተው ተኩስ ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ መደረጉና ወደ ማረሚያ ቤቱ መመለሳቸውን ገልጸዋል።