(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2011) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከሀሰት ዜና እና ከጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቀረበ።
ኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት ዘመቻ አትፈርስም ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አሁን በሃገሪቱ ላለው ውጥረት ግን መነሻ ምክንያት ነው ብሏል።
በዚህ የለውጥ ወቅት ግጭት በመቀስቀስና ብጥብጥ በማንገስ የህዝብ መፈናቀልና ስቃይን ለማባባስ በማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
አንዳንድ ሀላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ተመሳሳይ ስም እየተጠቀሙ ሀሰት እየነዙም ነው ብሏል
በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት ዜናዎችና የጥላቻ ንግግሮችን በስፋት በማሰራጨት ስሜት በመኮርኮር ላይ እንደሚገኙም ጠቅሷል።
ይህንን የታቀደና የተደራጀ ዘመቻ ዓላማ ያልተረዱ ወገኖች ተነካብኝ ያሉትን ወገን ሳያጣሩ በሚሰጡት አፀፋ ምላሽ ወደ ግጭት ሲያመሩ እና ሲተናኮሱ እንደሚስተዋልም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይህንን የሚሰሩና የሚቆሰቁሱ ደግሞ በሞቀ ቤታቸው ሆነው ሌላ ብጥብጥ ይጠነስሳሉም ነው ያለው፡፡
እናም ማህበራዊ ሚዲያ ብጥብጥና ፀብ በመፍጠር ለግጭት መንስኤ መሆኑን ቤሮው ገልጿል።
የአመራሮችንና የድርጅቶችን ስም በመጠቀም፣ ብሄር፣ ፆታ እና ቦታ በመቀየር የግጭት ድግስ የሚደግሱ መበራከታቸውን በመግለጽ።
በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም የበዙ የሐሰት መረጃዎች ይተላለፋሉ፤ ሐሰት ጮኾ ስለተነገረ፣ ጎልቶ ስለተጻፈ፣ በብዙ ሰዎች ስለ ተደገፈ ወይም በታዋቂ ሰዎች ስለተወራ እውነት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ግን የዘላለም እውነት ነች ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
ስለሆነም በማህበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መረጃዎችን መመርመርና ማስተዋል ይገባል ብሏል።የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በድረገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ።
ኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት ዘመቻ አትፈርስም ያለው የጠቅላይ ሚስትር ቢሮ አሁን በሃገሪቱ ላለው ውጥረት ግን መነሻ ምክንያት ነው ብሏል።