የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2011)የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ይህንኑ እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና ሌሎችንም ጨምሮ መንግስት ሕግን የማስከበርን ሃላፊነት እየተወጣ አይደለም ብለዋል።

የፓርቲው መግለጫ እንዳመለከተው እጅግ በርካታ ዜጎች መፈናቀል እየደረሳባቸው ነው።

መንግሥት የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደመኖሪያ ቀዬአቸውና ቤቶቻቸው ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ ወደ ብሔር ይዞታቸው \”የጎሣ ግዛታቸው\” መልሶ ለማቋቋም በሚያደርገው ትግል ተወላጆች ለኢኮኖሚ እና ለሥነ-ልቦና ችግር ተጋልጠዋልም ነው ያለው።

በጌዲኦ፣ ኦሮሞ ከሶማሌ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ማረቆ፣ መስቃን፣ ቅማንት፣ ሼኮ፣ ወዘተ የመሳሰሉት በኃይል እየተፈናቀሉና እየሞቱ ባሉበት – በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረት እንኳ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አለመኖሩም ነው የገለጸው።

፤ከሶማሌ ክልል ውስጥ ኦሮሞዎችን ለማስለቀቅና በአዲስ አበባ ክልል ለማስፈር የተደረገው ሙከራ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

እናም ይህ ማፈናቀልና ወዳልተፈለገ ስፍራ ማስፈር ሁሉም ዜጎች የመኖሪያ ቦታቸውን እንዲመርጡና በህይወት እንዲኖሩ የሚያደርጉትን ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ይጥሳል ነው ያለው።

ይሕ ድርጊት በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የአስተዳደርና የሥርዓት ንቅዘት ያሳያልም ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለጋጣፎ ከተማ የዜጎችን መኖሪያ ቤቶች በድንገት በማፍረስ እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውና ሕጻናትና እመጫት እናቶች ጭምር እላያቸው ላይ ቤት ስለመፍረሱ ሰምተን እጅግ አሳዝኖናል፣ አሳፍሮናልም ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ዜጎች ሀብት ማለት የሀገር ሀብት መሆኑን በቂ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ተግባር ነው ፡፡

እንደ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ  መግለጫ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በኮዬ_ፈጬ፣ ዜጎች ለዓመታት ባጠራቀሙት ገንዘብ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ደርሷቸው እንዳያገኙ መደረጋቸው የህግ የበላይነት መከበር ጥያቄ ያስነሳ ድርጊት ሆኗል፡፡

ህገ-መንግስታዊ ባልሆኑ ህዝባዊ አመራሮች እና ቡድኖች፡- ለምሳሌ: በአንቀጽ 49 (5) በግልጽ እንደተቀመጠው በአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ጉዳይ አለመግባባት ሊፈጠር አይችልም፡፡ በኦሮሞ ክልል ማዕከላዊ ቦታውን መጥቀስ እና በአገልግሎቶች እና አቅርቦቶች ተደራሽነት  የአዲስ አበባ ጉዳይም በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት መታየት ያለበት ጉዳይ እንደመሆኑ፣ ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች እየተቀሰቀሱ የሕዝባችንን ሰላማዊ ኑሮ እያወኩ ይገኛሉም ብሏል።

ስለሆነም የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት መታየት ያለበት ጉዳይ በመሆኑ  መንግስት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ኢሶዴፓ በመግለጫው አሳስቧል።