(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2011) በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈፀም ተጠርጥረው በቀረቡ ግለሰቦች ላይ በምስክርነት የቀረቡ ግለሰቦችን ፎቶ በማንሳት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ሲያሰራጩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ከፌደራል ፖሊስ ያገኘውን መረጃ ጠቀሶ ፋና እንደዘገበው ሁለቱ ግለሰቦች ወደ ፍርድ ቤቱ በድብቅ በመግባት ምስክሮችን ፎቶ በማንሳት በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ሲያሰራጩ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው በአሁን ወቅት ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።የሁለቱን ሰዎች ማንነት በተመለከተ ፖሊስ ከመግለጽ ተቆጥቧል
ተጠርጣሪዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በፍርድ ቤት ቅድመ መርመራ ላይ እያሉ ፎቶ በማንሳት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በማሰራጨት ስጋት ለመፍጠርና እንዲሸሹ ለማደረረግ መሞከራቸውን ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስም በአሁኑ ወቅት የምስክሮችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር በቂ ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክቷል ።