ሕወሃት 7 ሺ የልዩ ሃይል አባላቱን በራያ ኮረም አሰፈረ

    (ኢሳት ዲሲ–የካቲት 13/2019)  ሕወሃት 7 ሺ የልዩ ሃይል አባላቱን በራያ ኮረም አካባቢ ማስፈሩ ተነገረ።

ይህንኑ ተከትሎም የራያ ማንነት አስመላሽ አብይ ኮሚቴ እልቂት ከመፈጠሩ በፊት  የፌደራል መንግስቱ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል ።

ፋይል

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ37 ሺ በላይ የሚሆኑ የትግራይ ልዩ ሃይል በአካባቢው መስፈሩን ኮሚቴው አስታወቋል።

ይህ በእንዲህም ሕወሐት ሚሊሻዎቹን እያሰፈረ የሚገኘው ከክልል ሶስት ጋር ጦርነት ለማካሄድ እንደሆነ ከስልጠናው ጠፍተው የወጡ ሚሊሻዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የራያ ማንነት አስመላሽ አብይ ኮሚቴ ሕወሃት በራያና በአካባቢው ያለውን ችግር በተመለከተ ለፌደራል መንግስቱ አብተደጋጋሚ ልናሳውቅ ሞክረናል።

ነገር ግን ጉዳዩ ምንም ምላሽ ሳያገኝ አሁን የከፋ አደጋን ደቅኗል ይላሉ የራያ የማንነት አስመላሽ አብይ ኮሚቴ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ።

እንደ አቶ ደጀኔ አባባል ከሆነ የህወሃት ዝግጅት ሶስት ወር አልፎታል።በሳምንታት እንኳን በርካታ ሃይልን ሲያሰማራ አይተናል።

አሁን ይሄን መረጃ ለእናንተ እየሰጠሁ ባለሁበት ሰአት ህወሃት ሰራዊቱን ወደ ኮረም እያስገባ ነው ብለዋል።

አሁን በአካባቢው የተደቀነውን አደጋ የአማራም ሆነ የትግራይ ክልላዊ መንግስቶች የሚያስቆሙት አይደለም።

ስለዚህ የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የህወሃት ሰራዊት ስልጠና ዋነኛ አላማ ከክልል ሶስት ጋ ጦርነት ለመግጠም ነው ሲሉ የተናገሩት በስልጠናው ሲሳተፉ የነበሩና በኋላም ጠፍተው ከተመለሱት ሚሊሻዎች አንዱ ናቸው ለኢሳት መረጃውን የሰጡት።

እሳቸው እንደሚሉት ስልጠናውን ረግጠው እንዲወጡ ያደረጋቸው የራያ ማንነት የሚባል ጉዳይ ማንሳት አትችሉም የሚል ርዕስ ሲመጣ ነው።

አሁንም ህወሃት ወጣቱን መመልመል መቀጠሉን ይናገራሉ።አብዛኛው ሰልጣኝ ግን በግዴታ የሚሳተፍ መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም።

ሁለቱም ወገኖች በማያውቁት መንገድ እንዲያልቁ እየተደረገ ነው የሚመለከተው አካል ደግሞ ለዚህ አደጋ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።