(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2011)በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ሳቢያ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
በምትክ መልክ የተሰጣቸው የእርሻ መሬትም ከመኖሪያቸው 60 ኪሎ ሜትር በመራቁ በእጅጉ መቸገራቸውን አስታወቀዋል።
በጣና በለሰ ይሰራሉ የተባሉት ስኳር ፋብሪካዎችም እስካሁን ባለመጠናቀቃቸው ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸው መገለጹ ይታወሳል።
በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ በጣና በለስ ተፋሰስ ወስጥ ከስምንት ዓመታት በፊት አካባቢው ለስኳር ልማት በመፈለጉና ከልማቱ ተጠቃሚዎች ትሆናላችሁ በሚል ለነዋሪዎቹ ተስፋን በመስጠት እንዲነሱ መደረጉን አስተያየታቸውን ለበኩር ጋዜጣ የሰጡ ሰዎች ተናግረዋል።
ለፕሮጀክቱ ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተከለለ ሲሆን በፌደራል ደረጃ በስኳር ኮርፓሬሽን የበላይ ጠባቂነት ስራው ሲከናወን ቆይቷል።
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥራውን እንዲያከናውን ኃላፊነት ቢሰጠውም ከተባለው ግብ ላይ እስካሁን አልደረሰም፡፡
ባለፈት 7 አመታት ለስኳር ልማት ተተከለ የተባለው ሸንኮራ አገዳም ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ከ 7 ቢሊየን ብር በላይ የተፈጥሮ ስኳር ሳይመረት ባክኗል።
የተበላሸውን ሸንኮራ አገዳ ለማስወገድም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ አስወጥቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከነበራቸው ይዞታ በልማቱ ምክንያት ከተደላደለ ኑሯቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ለከፋ ርሀብ ተጋልጠዋል ነው የተባለው።
ሰሞኑን በአካባቢው የተገኙት የበኩር ጋዜጣ ባልደረቦች በስኳር ፕሮጀክቱ ምክንያት የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን መመገብ አቅቷቸዋል ብለዋል።
በዚህም የስኳር ልማት ፕሮጀክቱና ነዋሪው ሆድና ጀርባ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
የተሰጣቸው ምትክ የእርሻ መሬት እስከ ሁለት ቀን ድረስ የሚያስኬድ በመሆኑ በረሃብ ምክንያት ውድ ህይወታቸውን እስከመነጠቅ የደረሱ እንዳሉም የጋዜጣው ዘገባ አስረድቷል፡፡
ችግሩን በሚመለከት ቅሬታ ሲያቀርቡም ፀረ-ልማት በማለት እንደሚያሸማቅቋቸው ያስረዳሉ፡፡
በስኳር ፕሮጀክቱ ምክንያት ከመሬታቸው የተነሱ ነዋሪዎች በሚኖሩበት አልኩራንድ ቀበሌ በዕድሜ የገፉ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የተወሰኑት ነዋሪዎች ምትክ የእርሻ መሬት አልተሰጣቸውም፤ የእንስሳት የግጦሽ ቦታም አላገኙም፡፡
ይህን በተመለከተ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊና በነዋሪዎቹ ላይ የተከሰተውን ችግር የሚያጠናው ቡድን አባል አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሶስት ሺህ 200 ሰዎች ራሳቸውን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አረጋገጠዋል፡፡
የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ በበኩሉ የተነሳውን ቅሬታ ትክክል ነው ብሏል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ ዳምጤ የልማቱ ተነሽዎች “60 ኪሎ ሜትር ነው ለማረስ የሚሄዱት፤ አፈናቅሎ ማቋቋም ተገቢ አይደለም፡፡
መንገድ፣ ውኃ፣ መብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላት ነበረባቸው” ነው ያሉት፡፡
በወቅቱ ጥናቱ ሲካሄድ መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉ ታሳቢ መደረጉን ያስታወሱት አቶ መለሰ “በተግባር ሲታይ ግን በጥናቱ መሰረት አልተከናወነም”ብለዋል።
አቶ መለሰ “የስኳር ልማት ኮርፓሬሽን የአመራር ደካማነት ለዚህ ውድቀት አብቅቶናል” ብለዋል፡፡
ፈንድቃ ከተማ አካባቢ ለቱርኮች ተሰጥቶ የነበረ ሁለት ሺህ 500 ሄክታር እና ለባለሀብቶች ደግሞ 900 ሄክታር መሬት ባለመልማቱ መመለሱን ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ምትክ መሬት ላልተሰጣቸውና ቅሬታ ላላቸው ተነሽዎች ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡