በምዕራብ ጎንደር የተፈጸመው ግድያ ኃላፊነት የጎደለው ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/ 2011) በመከላከያ ሰራዊት አባላት በምዕራብ ጎንደር መተማ አካባቢ የተፈጸመው ግድያ ኃላፊነት የጎደለውና ትክክለኛ ያለመሆኑን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ እንዳርጋቸው ገለጹ።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስለጉዳዩ ትናንት በሰጡት መግለጫ  በደረሰው ጉዳት ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካል ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለም የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት ማጠናቀቁን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውም ታወቋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት ተሽከርካሪዎችን ከአንደኛው ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ በተሞከረበት ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል፡፡

ሁኔታው አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ምክንያት ይቅረብለት በዚህ ዓይነት የግጭት ወቅት ንጹኃንን መጠበቅና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባ እንደነበርም ነው የገለጹት።

በተፈጠረው ግጭት አሳዛኝ በሆነ መልኩ ንጹኃን ዜጎች ጭምር ሞተዋል፤ በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ቤተሰቦች በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እገልጻለሁ፤ መጽናናትንም እመኛለሁምብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ይህን ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ርምጃ መወሰድ አልነበረበትም።

ችግሩ ቢያጋጥም እንኳ እሑድና ሰኞ እንደተደረገው በትዕግስትና በውይይት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት መደረግ ነበረበትም ነው ያሉት፡፡

እናም ግድያው ኃላፊነት የጎደለውና ትክክለኛ ያለመሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  በደረሰው ጉዳት ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካል ኃላፊነት መውሰድ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

ግድያውን የሚያጣራ ቡድን ወደ አካባቢ በአስቸኳይ እንደሚላክም አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩ ተጣርቶ ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ ርምጃ የወሰዱ አካላት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖርም  ነው የገለጹት፡፡

በተያያዘ ሁኔታም በምዕራብ ጎንደር አካባቢ የእርስ በእርስ መገዳደል እየቀጠለ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ግድያው የአማራና የቅማንትን ሕዝብ ለአደጋ ያጋለጠ አደገኛ አካሄድ ስለሆነም በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል፡፡

ይሕ በእንዲህ እንዳለም የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት መጠናቀቁን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልሉ የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን በኩል መስራት አለባቸው ተብሎ የተማነባቸውን ጉዳዮች በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን የዕእከላዊ ኮሚቴው ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በሌላ በኩል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ታወቋል።

ፓርቲዎቹ አሁን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ታሳቢ ያደረገ የሁለትዮሽ ውይይት በሥራ አስፈጻሚዎቻቸው በኩል  በአዲስ አበባ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች፥ በጸጥታ ጉዳይ፣ በሠላምና ደህንነት፣ በልማትና የአማራ ህዝብ የጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል በተመረጡ ሥራ አስፈጻሚዎች በኩል የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል።