በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ አሸነፉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2011)በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በተካሄደ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ።

የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን ይፋ ከማድረጉ በፊት የሃገሪቱ መንግስት በርዕሰ መዲናዋ ኪንሻሳ አድማ በታኝ ፖሊሶችሽን ያሰማራ ሲሆን ውጤቱም የተገለጸው ከለሊቱ 9 ሰአት እንደነበርም ተመልክቷል።

ውጤቱ መገለጹን ተከትሎ የሚከተለውን አለመረጋጋት ለመግታት ሰው ከእንቅልፉ ሳይነቃ ውጤቱን መግለጽ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ከምርጫ ኮሚሽኑ መረዳት ተችሏል።

በአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ የሚደገፉት እጩ ከመራጩ ህዝብ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ድምጽ በማግኘት ሶስተኛ ሲሆኑ፣አሸናፊው ፊሊክስ ሲዲኮ 7 ሚሊየን የመራጮች ድምጽ ማግኘታቸው ታውቋል።

ይህም ከመራጩ ህዝብ የ38 ነጥብ 57 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ያሳያል ተብሏል።

ከመራጩ ህዝብ የ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ህዝብን ድምጽ በማግኘት የሁለተኝነት ደረጃን የያዙት ማርቲን ፋይሉ፣ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በርካታ ታዛቢዎችን ያሰማራችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በምርጫው ውጤት ላይ ጥያቄን አንስታለች።

አጠቃላይ ውጤቱ በቅርቡ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።

ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ የመጀመሪያው በተባለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለ18 አመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ጆሴፍ ካቢላ ከሳምንታት በኋላ ስልጣን ይለቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።