(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2011)የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ በድጋሚ መገታቱ ተሰማ።
የሽሬ ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ ማገታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በመንግስት ውሳኔ ሰራዊቱ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ቢሰጠውም ህዝብ መንገድ በመዝጋት የሰራዊቱን ግስጋሴ ማስቆሙ ታውቋል።
በርካታ የመከላከያ ተሽከርካሪዎች በሽሬ ከተማ በሚገኝ ስታዲየም እንዲገባ መደረጉ ተገልጿል።
የሽሬ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ተቃውሞ በማሰማት የመከላከያ ተሽከርካሪዎችና መሳሪያዎችን እንደማይለቁ አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ እንቅስቃሴው ሲስተጓጎል በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከዛላምበሳ ግንባር የተንቀሳቀሰውን የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ነዋሪዎች መንገድ ተዘግቶበት ለሁለት ቀናት መታገቱ የሚታወስ ነው።
ድንበሩን ክፍት አድርጎ መሄዱ ለጥቃት ይዳርገናል በሚል አቋም ተተኪ ሰራዊት ካልመጣ መከላከያ ሰራዊት አይወጣም በሚል በድንጋይ መንገድ በመዝጋት ያገተው የዛላምበሳ አካባቢ ነዋሪ በመጨረሻም መንግስት ጉዳዩን እልባት በመስጠት ሰራዊቱ መንቀሳቀስ ችሏል።
ይህን በተመለከተ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰራዊት የማንቀሳቀስም ሆነ የማቆም መብት ያለው የፌደራል መንግስቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጊቱ ተገቢ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በህዝቡ የቀረበውን ስጋት በማንሳት የትግራይ ጥቃት የሌላው ኢትዮጵያዊም ጥቃት በመሆኑ ሌላውንም ይመለከታል ብለዋል።
መንግስት በጉዳዩ ላይ አቋሙን በግልጽ እያሳወቀ ባለበት በዚህን ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ የመከላከያ ሰራዊቱ እንቅስቃሴ በተቃውሞ መገታቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
በትግራይ ሽሬ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ የነበሩና መሳሪያ የጫኑ በርካታ የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች በሽሬ ከተማ ነዋሪዎች መንገድ ላይ እንዲቆሙ ተደርገዋል።
በኋላም ወደ ሽሬ ስታዲየም እንዲገቡ መደረጋቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
የተሽከርካሪዎቹን ግስጋሴ የገታው ነዋሪ በሽሬ ስታዲየም በማምራት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደነበርም ታውቋል።
ነዋሪዎቹ መከላከያ ሰራዊት መውጣት የለበትም ያሉ ሲሆን በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ያነጣጠረ የተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የመከላከያ ሰራዊቱ ተሽከርካሪዎች በሽሬ ስታዲየም እንደሚገኙና ህዝቡ ተቃውሞውን በመቀጠል የመንግስት ሰዎች እንዲያነጋግሯቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
በጉዳዩ ላይ መከላከያ ሚኒስቴርን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በሀገር መከላከያ ሚኒስትር የመረጃና ትንተና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል መላኩ ሽፈራው እንዲህ ዓይነት ድርጊት ህገመንግስቱን የሚጥስ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።