ሳውዲ የሴቶችን መብት የሚጠብቁ ተጨማሪ ርምጃዎችን ተግባራዊ አደረገች

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 29/2011) የሳውዲአረቢያው አልጋወራሽ የሴቶችን መብት የሚጠብቁ ተጨማሪ ርምጃዎችን ተግባራዊ አደረጉ።

የሳውዲ አረቢያ ሴቶች ጋብቻቸው መፍረሱን የሚያውቁበት ዕድልና መብት ተነፍገው ቢቆዩም ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው መመሪያ ወንዱ ጋብቻውን አልፈልግም ብሎ ፍቺ ሲጠይቅና ሲፈጸምለት ለባለቤትየው ትዳርሽ ፈርሷል የሚል የጽሁፍ መልዕክት እንዲደርሳት ተወስኖ ተግባራዊ ሆኗል።

ፋይል

ቀደም ብሎ በነበረው አሰራር ሴቷ ትዳርዋ ይፍረስ አይፍረስ የምታውቅበት ሁኔታ አልነበረም።

በሳውዲ አረቢያ ከትናንት ጀምሮ ማሻሻያ የተደረገበት ይህ አሰራር በብዙ የአረብ ሃገራት አሁንም እየተሰራበት መሆኑን ሳውድ አቡዳይሂ የተባሉ የመብት ተሟጋች ለአልጀዚራ ገልጸዋል።

የ33 ዓመቱ የሳውዲ አረቢያው አልጋወራሽ ሙሃመድ ቢን ሰልማን የሳውዲ አረቢያን የፖለቲካ አመራር ከያዙበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀድን ጨምሮ መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የሳውዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን የለውጥ ርምጃዎችን ከመጀመራቸው በፊት በሳውዲ አረቢያ ሴቶች መኪና ማሽከርከር ተከልክለው ቆይተዋል።

ስፖርታዊ ውድድሮችን ለመመልከት ስታድየም መግባት እንዲሁም በምርጫ ወቅት በመራጭነት መሳተፍም ሳይችሉ ቆይተዋል።

እነዚህ የተዘረዘሩ ገደቦችን በማንሳት የሴቶችን መብት እያስጠበቁ የቀጠሉት መሃመድ ቢን ሰልማን ርምጃቸው በአባታቸው በሳውዲ አረቢያው ንጉስ ሰልማን ቢን አብድል አዘንታ ሙሉ ፈቃድ እየተፈጸመ መሆኑም ተመልክቷል።

ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ሴቶች ትዳራቸው መፍረሱን እንዲያውቁ የጽሁፍ መልዕክት የማድረሱ ርምጃ የሚበረታታ ቢሆንም እጅግ ብዙ ይቀረዋል ሲሉ የመብት ተሟጋቾች አስተያየት ሰጥተዋል።

ኢኳሊቲ ናው የተባለ የመብት ተሟጋች ድርጅት አባል ለአልጄዚራ በሰጡት አስተያየት ሴቶቹ ትዳራቸው መፍረሱን እንዲያውቁ ቢደረግም ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጡ የመብት ጥያቄዎችን መመሪያው አይመልስም ብለዋል።

የሳውዲ አረቢያ ሴቶች በአለባበስ ላይ የተጣለውን ገደብ ጨምሮ አሁንም ተጨማሪ ርምጃዎችን በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

የሳውዲ አረቢያ ሴቶች ጋብቻ ለመፈጸም የቤተሰባቸው አባል ከሆነ ወንድ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ለስራ ለጉዞም ሆነ ህክምና ለማግኘት የሳውዲ አረቢያ ሴቶች የባላቸውን ካላገቡ ደግሞ የቤተሰባቸው አባል የሆነ ወንድ ሰው ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

እነዚህ ሁሉ ገደቦች እንዲነሱ የመብት ተሟጋቾች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።