ታህሳስ 24 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በ”ማርች ፎር ፍሪደም”ና በሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አስተባባሪነት በየወሩ በአሜሪካን ፕሬዚዳንት መኖሪያ ፊት ለፊት የሚካሄደውና በኢትዮጵያ የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን የሚያስበው የሻማ ማብራት ስነስርአት በሞቀ ሁኔታ ተካሂዷል።
እስክንደር ነጋ እና አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ለሶስተኛ ግዜ በተካሄደው የሻማ ማብራት ስነስርአት ላይ አያሌ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን፡
የአሜሪካን መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ፖሊሲ እንዲቀይር የሚጠይቁና የኢህአዴግ ህወሀት መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ባስቸኳይ እንዲፈታ የሚያሳስቡ መፈክሮች ተሰምተዋል።
በዚህ ከዋይት ሀውስ አጥር ስር በተካሄደ ሰልፍ ላይ ሴቶችና ወጣቶች በብዛት መገኘታቸውን፣ ዝናብና ብርድ ያልበገራቸው ተሰላፊዎቹ በታላቅ መንፈስና መነሳሳት መፈክሮችንና ጣእመ ዜማዎችን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የሰልፉ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ካሳ አያሌው፡ በሚቀጥለው ወርም ተመሳሳይ የሻማ ማብራት ስርአት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የመለስ መንግስት የፖለቲካ ተቺዎችንና ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት ወንጀል መክሰሱ አለማቀፍ ውግዘት እያስከተለበት ነው።
ተመልካቾቻችን በዋሽንግተን የተካሄደውን የሻማ ማብራት ስነስርአት አስመልክቶ የተቀናበረውን ዘገባ ከዜናው በማስከተል እናቀርባለን።