“ ከአሁን በሁዋላ የኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ከሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ጉዳይ ተለይቶ የሚታይ አይደለም” ሲሉ አቶ አሚን ጁንዲ ገለጹ

ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዋና ፀሀፊ የሆኑት አቶ አሚን ይህን ያሉት፤ የድርጅታቸውን አዲስ የፕሮግራም ለውጥ አስመልክቶ ከህብር ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።
አዲሱ አቋማችሁ በአቶ መለስ ስርዓት ላይ ከሚፈጥረው ጫና አኳያ እንዲሁም እየለወጣችሁት ያላችሁት ለረዥም ጊዜ ስታራምዱት የቆያችሁትን አቋም ከመሆኑ አንፃር ከውስጥም ከውጭም ተቃውሞ ቢነሳባችሁ ምን ያህል ተዘጋጅታችሁዋል? በማለትም የራዲዮው አዘጋጅ  ለአቶ አሚን ጥያቄ  ያቀረበላቸው ጉባኤያቸውን ከሁለት ቀናት በፊት ሲያጠናቅቁ  ነበር።
የግንባሩ ዋና ፀሀፊ አቶ አሚን ለጥያቄው በሰጡት ምላሽም፤ሁልጊዜም አዲስ ነገር በሚመጣበት ጊዜ ተቃውሞ መነሳቱ የሚጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል። 
ይህን ውሳኔ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር  አጥብቆ መቃወሙ ይታወሳል።
ይሁንና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ  በርካታ ኢትዮጵያውያን  በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር  ይፋ ያደረገውን አዲስ አቋም ተከትሎ ደስታቸውን እየገለጡ ነው።
በኢሳት የኢሜል ሳጥን ውስጥ የተቀመጡ መልእክቶች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች በውሳኔው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ያለፉትን የስነ ልቦና ጠባሳዎች ለማስተካከል ድርጅቱ በርካታ ስራዎች እንደሚጠብቁት ሳይገልጡ አላለፉም።