(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 5/2011) ከሃገር ሲያመልጡ ድንበር ላይ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠየቁ።
በቢሊየን ብር ምዝበራና ብክነት ተጠያቂ ነዎት በሚል ፍርድ ቤት የቀረቡት ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው የጠየቁት አቅም የለኝም በሚል መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሰብአዊ መብት ረገጣና መሰል ወንጀሎች ከሚፈለጉት አንዱ የሆኑት አቶ ያሬድ ዘሪሁንን አስመልጠዋል የተባሉ ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተመልክቷል።
ከሃገር ሊያመልጡ ሲሉ ትላንት ሁመራ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከወንድማቸውና እንዲሁም የኢቲቪ ጋዜጠኛ ከነበረችው ፍጹም የሺጥላ ጋር ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ፈጸሙት የተባለው ወንጀል በዝርዝር ቀርቧል።
የቀድሞው የሜቴክ ሃላፊ ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በጡረታ የማገኘው 4ሺ ብር ብቻ ስለሆነና ሌላም ገቢ ስለሌለኝ መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ ሲሉ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ መንግስት ጠብቃ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ ሰቷል።
የጄኔራሉ ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘውም በተመሳሳይ አቅም ስለሌለኝ ጠበቃ ይቁምልኝ ማለታቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበረችው ፍጹም የሺጥላም ከሜቴክ የሌብነት ወንጀል ጋር በተያይዘ ተጠርጥራ የታሰረች ሲሆን አብራ ፍርድ ቤት ቀርባለች።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና አባሪዎቻቸው በተለዋጭ ቀጠሮ ለነገ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተወስኖ ወደ ወህኒ ቤት ተመልሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ ሃላፊ በኋላም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ ያሬድ ዘሪሁን አስመልጠዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል።
በማስመለጥ የተባበሩት ሹፌራቸውና የነፍስ አባታቸው መሆናቸውም ተመልክቷል።
አቶ ያሬድ ዘሪሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ኣንደያዙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።በአጭር ጊዜም ከስልጣን ተነስተዋል።
ለረጅም አመታት በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም ውስጥ በሃላፊነት ማገልገላቸውም ታዉቋል።
ባለፈው ቅዳሜ በወረዳ 23 ቀበሌ 12 የሚገኘውና በቤት ቁጥር 177 የተመዘገበው የአቶ ያሬድ ዘሪሁን መኖሪያ ቤት መበርበሩን ሰኞ ዕለት መዘገባችን ይታወሳል።