በሕገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ይቀጥላል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 5/2011) በሕገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የክልል መንግስታትም በህገ ወጦች ላይ የሚወሰደውን ርምጃ በመደገፍ መግለጫ አውጥተዋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ከእንግዲህ የህዝቡ ቅሬታ  ምላሽ ሳያገኝ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ የለም።

ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታና እሮሮ ከሚሰማባቸው ውስጥ ሀገራዊ የፍትህ ስርዓቱ በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር ሊያስቆም አለመቻሉ ይገኝበታል ብሏል።

የሀገራችንን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዱ አሻጥሮች ሲፈፀሙ፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በግላጭ ሲጣሱ እንዲሁም መንግስታዊ ስልጣን ለሽብር ተግባር ማስፈፀሚያ ሲውል ቆይቷል።

እናም በሕገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በቅርቡም የተሰጣቸውን መንግስታዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ወደጎን በመተውና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በአስከፊ የምዝበራ፣ የሰብዓዊ ጥሰትና የሽብር ተግባር ስለመሳተፋቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ህጋዊ መንገዱን በመከተል በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያለው።

ጽናም መላው የድርጅቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም  ህዝቡ በዚህ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከመንግስት ጎን ቆሞ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ኢሕአዴግ ጥሪ አቅርቧል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለም የፌዴራል መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እንደሚደግፍ ገልጿል።

የህዝብን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋል ከሀገር ክህደት ተለይቶ እንደማይታይም መግለጫው አትቷል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዛሬ ባወጣው መግለጫው፥ የኢፌዴሪ መንግስት በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ እና በሀገሪቱ ላይ ከባድ የሙስና የወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ የበላይነት አንዲከበር እየሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ ነው ።

በተያያዘ ዜና መንግስት በማስረጃ በመደገፍ የሌብነትና ሃገር የማራቆት ወንጀልን ለማስቆም የሄደበት በሳልነት የተሞላበት  መንገድን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእጅጉ እንደሚያደንቅ ገልጿል፡፡

ክልሉ የሚጠበቅበትን ማንኛውንም ህጋዊ ትብብር ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑንም በኮሚኒኪሽን ጽሕፈት ቤት በኩል ገልጿል፡፡

የትግራይ ህዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር መሆኑን ደግሞ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቋል።

ይሕም ሆኖ ግን ችግሩ በእኩል እንዲስተናገድ ከማድረግ ባለፈ እርቅና ይቅር ባይነትን መሰረት አድርጎ የተጀመረው ሂደት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።

“የህግ የበላይነትም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚጥይቅ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ያምናል” ሲል በእፈጻጸሙ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ገልጿል፡፡