የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበውን የስደተኞች ዕቅድ የሊቢያ መንግስት ውድቅ አደረገ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 09 ቀን 2011 ዓ/ም ) የአውሮፓ ኅብረት ከኅብረቱ ግዛት ውጪ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያን ለማቋቋም ያቀረበውን ዕቅድ እንደማይቀበሉት የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚንስት አስታወቁ።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የጣሊያን መንግስት የስደተኞች ፍልሰት ቁጥጥር እንዲደረግበት ላቀረበው ሃሳብ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ቁጥጥሩን ለማጥበቅ የወሰኑትን ውሳኔ ተከትሎ የተወሰደ ነበር።
ነገር ግን የሊቢያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሀመድ አል-ጣሂር ጠቅሶ የኦስትሪያው ጋዜጣ እንዳለው ሁሉም የሰሜን አፍሪካ አገራት ዕቅዱን ውድቅ በማድረግ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሊቢያ በደቡባዊ ግዛቷ በኩል ካሉት አጎራባች አገራት ጋር ብቻ የድንበር ትብብር ሥምምነት እደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አክለው ገልጸዋል።
የፈረንሳይ ርዕሰ ብሄር ኤማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበው ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሰሜን አፍሪካ አገራት ፈቃደኝነታቸውን እስካላሳዩ ድረስ ውጤታማ ሊሆን አይችልም ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።