የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን ፖሊስ ገለፀ። አቶ አብዲ መሀመድ በእስር ቤት የሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ተናገሩ።

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን ፖሊስ ገለፀ። አቶ አብዲ መሀመድ በእስር ቤት የሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ተናገሩ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 09 ቀን 2011 ዓ/ም ) በጅግጅጋና አካባቢው ለተቀሰቀሰው የእርስበርስ ግጭቶች፣ የጅምላ መፈናቀል፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል፣ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ በመስጠት የዜጎችንና የአገር ሰላምን አውከዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀመድ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታወቀ።
ተጠርጣሪው አቶ አብዲ መሀመድ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ሲባል የፖሊስ ቢሮ ውስጥ ታስረው እንደነበርና በወቅቱም የእስር ቤቱን የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸውን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ የክስ ቻርጅ አቅርቧል።
ተከሳሹ አቶ አብዲ መሀመድ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ያቀረበባቸውን ክስ አለመፈጸመባቸውንና ፖሊስ በተቀነባበረ መልኩ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት ያደረገው ሴራ ነው ሲሉ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንን ጠቅሰው የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል። በተጨማሪም አንድ እስረኛ የሽንት ቤት በር ገንጥሎ እላያቸው ላይ በመጣል ጉዳት ሊያደርስባቸው መሞከሩንና የታሰሩበት እስር ቤትም የማይመችና የጤናቸው ሁኔታ ሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ለችሎቱ አሳውቀዋል።
ተጠርጣሪው ማንኛውም እስረኛ በሚቆይበት እስር ቤት ውስጥ መታሰራቸውን፤ በእርሳቸው ላይ በተለየ ምንም ዓይነት ጫና አለመደረጉንና በግል ውይይት ባደረጉበት ወቅት ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ መሆናቸውንና በዚህም ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቃቸውን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። በአብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ እንዲረዳው የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም ከሳሽና ተከሳሽ ያቀረቡትን አቤቱታ ካደመጠ በኋላ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የ10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመቀበል ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።