(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011) የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ከእስር ቤት ሊያመልጡ ሙከራ ማድረጋቸውን ፓሊስ ለፍርድ ቤት ተናገረ።
ፓሊስ በአቶ አብዲ ኢሌ ላይ ባደረገው ምርመራም በሶማሌ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ መሆናቸውን ማመናቸውንና ለዚህም ይቅርታ መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌ መሃመድ ክልሉን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ክልሉን እንደፈለጋቸው ሲያሽከረክሩና ተቆጣጣሪ የሌላቸው በሚመስል መልኩ ዜጎችን በመግደል፣በማሰርና ክልሉን ለቀው እንዲሰደዱ በማድረግ አምባገነንነታቸው ሲነገር ቆይቷል።
ከህወሃት አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ክልሉን ሲያሽከረክሩ የነበሩት አቶ አብዲ ኢሌ በአወዛጋቢነታቸውም ይታወቃሉ።
የህወሃት አገዛዝ ከቤተመንግስት መውጣቱን ተከትሎ በክልሉ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለመቀልበስ በርካታ ርምጃዎች ወስደዋል።
በተለይ የሶማሌ ክልል ወጣቶችን በማደራጀት ከሐምሌ 26/2010 እስከ ሐምሌ 30/2010 በክልሉ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፣በሚሊዮን ተፈናቅለዋል፣ አብያተ ክርስትያኖች ተቃጥለዋል።
በዚህም ምክንያት አቶ አብዲ ኢሌ ለእስር ተዳርገው ጉዳያቸው በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
አቶ አብዲ ኢሌ ለእስር ከተዳረጉበት ግዜ ጀምሮ የሰብአዊ መብታቸው እንደተጣሰና የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ መክረማቸው ይታወቃል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ምቹ ባልሆነ እስርቤት ታሰርኩ የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ለጤንነታቸው ሲባል በፓሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ፓሊስ ገልጿል።
ነገር ግን የታሰሩበት ክፍል መስኮት መስታወት በመስበርና የጥበቃ ሰራተኛን በማነቅ ሊያመልጡ መሞከራቸውን ለፍርድ ቤቱ ፖሊስ አስታውቋል።
አቶ አብዲ ኢሌ ግን የተጠቀሰባቸውን ውንጀላ የሀሰት ነው መሆኑንና ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑንም ለፍ/ቤት ተናግረዋል።
ፓሊስ በአቶ አብዲ ኢሌ ላይ ባደረገው ምርመራ በሶማሌ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ መሆናቸውን ማመናቸውንና ለዚህም ይቅርታ መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ የ10 ቀናት ግዜ እንዲፈቀድለት በመጠየት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጥሮ ተይዟል።